በጋዜጣው ሪፖርተር
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ፣ ከኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ቀኖና እና ሥርዓት ውጭ በሆነው ሁኔታ ‹‹እገሌ ተሐድሶ ነው››፤ ‹‹እገሌ መናፍቅ ነው›› የሚል እንቅስቃሴ፣ ከሐምሌ 25 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ ሕገወጥ መሆኑን እና ጥብቅ ቁጥጥርም እንደሚካሄድበት አስታወቁ፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ አረጋግጦ ካልወሰነ በስተቀር ከዚህ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚካሄድበትም ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ በወቅታዊ የቤተክርስቲያን ሁኔታ ላይ ተመሥርተው ሐምሌ 25 ቀን 2003 ዓ.ም. በቁጥር ል/ጽ/598/755/ዐ3 በኢትዮጵያና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ አህጉረ ስብከት ባስተላለፉት መመሪያ እንደተመለከተው ከቤተክርስቲያኒቱ ቀኖና እና ሥርዓት ውጭ በሆነ ሁኔታ እገሌ ተሐድሶ ነው፤ እገሌ መናፍቅ ነው የሚል ጽሑፍ ሲበተን ይታያል፤ ከዚህም ጋር በካሴት በሲዲ እና በመሳሰሉት መሣሪያዎች ሲሰራጭ ይስተዋላል፡፡
የሃይማኖት ሕጸጽ ሲያጋጥም ስለእውነትነቱ በሕጋዊ ማስረጃ የተደገፈ ጽሑፍ ቀርቦ፣ በሊቃውንት ጉባኤ ተመርምሮና ተጣርቶ ትክክለኛ መሆኑ ሲረጋገጥ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ታይቶ የመጨረሻ ውሳኔ ማግኘት እንዳለበት ቀኖና ቤተክርስቲያን እንደሚያዝ ያመለከቱት ፓትርያርኩ፣ ከጥንት ጀምሮ ሲሠራበት የነበረ አሠራርም ይህ እንደሆነ በአርዮስ፣ በመቅዶኖዮስ እና በንስጥሮስ ላይ የተላለፈው ሲኖዶሳዊ እና ቀኖናዊ ውሳኔ ማስረጃ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
‹‹ይህን መርሕና ቀኖና ቤተክርስቲያን ተከትሎ ውሳኔ ባልተሰጠበት ሁኔታ በግል ስሜትና ቀኖናው በማይፈቅደው ሁኔታ የግለሰቦችን ስም ማጥፋት በስም አጥፊነት በሕግ ከማስጠየቅ ያለፈ ሌላ ፋይዳ አይኖረውም›› ብለዋል፡፡
ሕግን፣ ሥርዓትንና የሥልጣን ገደብን ጠብቆ የማይፈጸም ድርጊት የምእመናን ህሊና በማሻከር በቤተክርስቲያኒቱ የአስተዳደር ሥርዓትና በአገሪቱ ሰላም ላይ እንቅፋት ለመፍጠር ሆን ተብሎ የሚደረግ ሙከራ መስሎ ስለሚታይ፤ ጐጂነቱ ቀላል አለመሆኑን የገለጹት አቡነ ጳውሎስ፣ የቤተክርስቲያኒቱ ተከታዮች የሆኑ ምእመናንና ምእመናት በተሳሳቱ ግለሰቦች አድራጎት እንዳይማረኩ አሳስበዋል፡፡ ቀደም ባሉት ዘመናት በመምህራንና በንስሐ አባቶች ጥብቅ ክትትልና ጥበቃ ሲደረግ መኖሩን የጠቆሙት ፓትርያርኩ ዛሬም ቢሆን የቤተክርስቲያኒቱን ሃይማኖትና ቀኖናዊ ሥርዓት የሚጥስ፣ አንድነትዋንም የሚያደፈርስ፣ ሰላምን የሚያሳጣ አዝማሚያ የሚታይበት ሁኔታ ሲያጋጥም ቸል የተባለበት ጊዜ አለመኖሩን፣ መኖርም እንደሌለበት ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ቀኖናው በማይፈቅደው አካሄድና በሌለው ሥልጣን ራሱ ወስኖ ከመሮጥ ይልቅ፣ የእምነት ሕጸጽ በትክክል አጋጥሞ ከሆነ በቂ ማስረጃ አለኝ የሚል ካለ፣ አለኝ የሚለውን ማስረጃ ቀኖናው በሚፈቅደው መርሕ መሠረት ለቅዱስ ሲኖዶስ ማቅረብ እንደሚኖርበት ፓትርያርኩ አስታውቀዋል፡፡
በዚህ ሁኔታ ሥርዓትንና ቀኖና ቤተክርስቲያንን በመጠበቅ የሚቀርብ ማስረጃ ካለ እንደጌታችን ትምህርት ተደጋጋሚ ምክር፣ ትምህርትና ተግሣጽ መስጠቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የማይታረም እና የማይመለስ ሆኖ ሲገኝ፣ በሕገ ቤተክርስቲያን መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ከመስጠት ወደኋላ እንደማይል ሁሉም ሊረዳ እንደሚገባ አቡነ ጳውሎስ አስገንዝበዋል፡፡ የሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት እንዲህ ዓይነቱ ችግር ሲያጋጥመው ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለሚመለከተው የቤተክርስቲያኒቱ የበላይ አካል አቅርቦ፣ ቅዱስ ሲኖዶስም አረጋግጦ ሲወስንና አውግዞ ሲለይ ካልሆነ በስተቀር፣ ከዚህ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ የቤተክርስቲያንንና የአገርን ሰላም ለማወክ የሚደረግ አካሄድ መሆኑ ታውቆ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንዲደረግም አሳስበዋል፡፡
ፓትርያርኩ ያስተላለፉትን መመሪያ ተከትሎ ባለፈው ረቡዕ ሐምሌ 27 ቀን 2003 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ አዳራሽ የአዲስ አባባ ገዳማትና አድባራት አለቆችና ጸሐፊዎች፣ ሰባክያነ ወንጌል በተገኙበት መግለጫ መሰጠቱን፣ ከስብሰባው በኋላም በተለያዩ መንገዶች ስማችን ጠፍቷል በሚል የሰባክያንና መዘምራን ተወካይ የሆኑ ለፓትርያርኩና ለቅዱስ ሲኖዶስ አቤቱታ ማቅረባቸውን፣ ‹‹ተሐድሶ በሚል የአየር ላይ ስም አደጋ ላይ የወደቁትን የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ቅዱስ ሲኖዶስ መፍትሔ እንዲሰጣቸው እንጠይቃለን፤›› ማለታቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ምንጭ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ እሑድ ነሐሴ 1 ቀን 2003 ዓ.ም. ገጽ 3
ይህን መመሪያ ተከትሎ ፀረወንጌል እንቅስቃሴው እክል እየገጠመው ያለውና እርስበርሱ እየተባላ የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን፣ የውስጥ ችግሩን አቅጣጫ “ተሐድሶ” እያለ ወደሚጠራቸው ወገኖች በማዞር፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ ያወጡትን መመሪያ በስውርም በግልጽም ተቃውሟል፡፡ በሐመር መጽሔት የነሐሴ 6/2003 ዓ.ም. ዕትም ላይ፣ “ሐሰት አንናገርም፤ እውነትንም አንደብቅም” በሚል ርእስ ያስነበበው ጽሑፍ ስም ሳይጠቅስ፣ “በቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር ውስጥ ያሉ አንዳንድ አካላት ‘ተሐድሶ የለም’ በሚለው ሐሳብ ተስማምተው በአንዳንድ መድረኮች በቀጥታና በተዘዋዋሪ ይህንኑ አስተሳሰብ የሚያጸና አስተያየት ሲሰጡ መታየታቸው” ያሳዘነው መሆኑን ገልጿል፡፡ ምንጭ አባ ሰላማ . ኦርግ