Monday, April 25, 2011

የማያስተውል ሕዝብ ይገለበጣል

<<የማያስተውል ሕዝብ ይገለበጣል>>

ሁላችንም እንደምናውቀው የመገልበጥ አደጋ እጅግ ትልቅ ጉዳት ያለው ነው፡፡ በዓለማችን ላይ በዚህ አደጋ ምክንያት ብዙ ጉዳቶችን አይተናል፡፡ በአገራችንም የወቅቱ አሳሳቢ ጉዳይ በተሽከርካሪ አማካይነት የሚደርሰው የግጭትና የመገልበጥ አደጋ ነው፡፡
ሕይወት ሲጠፋ፣ ንብረት ሲወድም፣ አካል ጉዳተኝነት ሲጨምር ማየትና መስማት የጆሮአችን ቀለብ ከሆነ ሰንብቷል፡፡ ይህ አደጋም የሚከሰተው ማስተዋል በጎደላቸው አሽከርካሪዎች ምክንያት መሆኑ ግልጽና የሚታወቅ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በአገራችን ተሽከርካሪን መጠቀም ትልቅ ሥጋት እየፈጠረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ መንግሥትም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ እርምጃዎችን ቢወስድም የሕግ አንቀጾች ቢረቀቁም አደጋው ግን በቊጥር ይቀንስ እንጂ ሥጋቱ አልቀረም፡፡
የዚህ አደጋ ትልቁ መንስኤ የማያስተውሉ አሽከርካሪዎች መብዛታቸው ነው፡፡ እንግዲህ አለማስተዋል ለመገልበጥ አደጋ ይዳርጋል፡፡ መፍትሔውም ማስተዋል ብቻ ነው፡፡ ውድ ሕይወትን እንዲሁም ዋጋ ያለው ንብረትን ለከፋ አደጋ ላለመዳረግ ማስዋል ትልቁ ቁልፍ ነው፡፡
ነቢዩ ‹‹የማያስተውል ሕዝብ ይገለበጣል›› በማለት ይናገራል፡፡ ለካስ ወገኖች! በመንፈሳዊውም ዓለም ትልቅ የመገልበጥ አደጋ አለ፡፡ ይህ አደጋም የሚከሰተው እንዲሁ ባለማስተዋል ነው፡፡ ነቢዩ ይህንን በተናገረበት ምዕራፍ ላይ የእስራኤል ሕዝብ ስለነበረበት መንፈሳዊ ውድቀት አስቀድሞ በመግለጥ ነው፡፡ ምዕራፉ ሲጀምር እንዲህ ይላል፡ - ‹‹ እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፡- እውነትና ምሕረት እግዚአብሔርን ማወቅ በምድር ስለሌለ እግዚአብሔር በምድር ላይ ከሚኖሩ ጋር ክርክር አለው፡፡›› (ሆሴ. 1÷ 1)
ለዚያ ሕዝብ መገልበጥ ምክንያት እውነትና ምሕረት እግዚአብሔርም ማወቅ አለመኖሩ ነው፡፡ ከእውነት ይልቅ ለሐሰትና ለስህተት ከምሕረት ይልቅ ለፍርድና ለነቀፋ እግዚአብሔርን ከማወቅ ይልቅ ስለሰዎች ለማወቅ የሚኖር ሕዝብ ትልቅ የመገልበጥ አደጋ እንደሚደርስበት ቃሉ ያረጋግጣል፡፡ የክርስትናው መሠረት እውነትና ምሕረት እንዲሁም እግዚአብሔርን ማወቅ ነው፡፡
እውነት፡ - የአምልኮ መሠረት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ 4 ÷ 24 ላይ እንደተናገረው እግዚአብሔርን ማምለክ በእውነትና በመንፈስ ነው፡፡ ሕዝብንም አርነት የሚያወጣው እውነት ነው፡፡ ቃሉም ‹‹እውነት አርነት ያወጣችኋል›› (ዮሐ. 8÷32) ይላል፡፡ እግዚአብሔርን በልማድ፣ በሥርዓትና በስሜት ለማምለክ የምናስብ ከሆነ ክርክራችን ከእግዚአብሔር ነው፡፡ ልማዳችንም ሆነ ሥርዓታችን ፋይዳ የሚኖረው አምልኮአችን እውነት ላይ ሲመሠረት ነው፡፡ ያለበለዚያ በአሸዋ ላይ እንደተመሠረተው ቤት የወሬ ንፋስና የመከራ ወጀብ በመጣ ጊዜ ቤቱ አደጋ ላይ መውደቁ አይቀርም፡፡
ምሕረት፡- ከእግዚአብሔር ባሕርይ አንዱ ምሕረት ነው፡፡ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለው መልካምነት ነው፡፡ መጽሐፉ እንደሚነግረን እርሱ ለክፉዎችና ለመልካሞች ፀሐይንና ዝናብን ያለ ልዩነት ይሰጣል፡፡ እኛ ብንሆን ግን ለጠላነውና ለወደድነው በፈረቃ እናከፋፍል ነበር፡፡ ከእርሱ የምንማረው ግን ለምንጠላቸው እንኳ መልካምነት እንደሚገባ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ግን የሚወዱንን እንኳ መውደድ እያቃተን ነው፡፡
እግዚአብሔርን ማወቅ፡- እግዚአብሔርን ማወቅ የክርስትናው ዐቢይ ነገር ነው፡፡ የማናውቀውን አምላክ እንዴት ልናመልክ እንችላለን? ብዙዎች ግን ሳያውቁት ያመልኩታል፡፡ ጳውሎስ በአቴና ሳለ የአቴና ሰዎች ሳያውቁት መሠዊያ ሠርተው የሚያመልኩት አምላክ እንደነበራቸው አየና የማያውቁትን አምላክ ማምለክ ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ ብቸኛውን አምላክ አስተዋወቃቸው፡፡ ዛሬም ብዙዎች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አያውቁትም ግን በስሙ ይጠራሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያንን አያውቋትም ግን ስለእርሷ ይሟገታሉ፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች ለመሆናቸውም የሕይወት ምስክርነት የሌላቸው ናቸው፡፡ ወገኖቼ! ይህ ቃል እኛን ኦርቶዶክሳውያንን ይመለከታል፡፡ የአብዛኛው ሕዝባችን መንፈሳዊ ሕይወት በእነዚህ መሠረቶች ላይ የቆመ አይደለም፡፡ ሆሳዕና! ብሎ ለማመስገን የሚቸኩል ዳግመኛም ስቀለው! ለማለት የማይዘገይ እንደ ውሃ በቀደዱለት ቦይ የሚፈስ ነው፡፡ ነገር ግን ወገኖቼ! ለማመስገንም ለመርገምም አንቸኩል፡፡ የምንሰማውንና የምናየውን በማስተዋል እንመርምር፡፡ ቃሉ ‹‹የማያስተውል ሕዝብ ይገለበጣል›› ይላልና፡፡
የእስራኤል ሕዝብ የተነቀፈው መሠረታዊ የእምነት መገለጫውን በማጣቱ ነው፡፡ ያለ እውነት ልናመልክ አንችልም፡፡ ያለ ምሕረት (በጎነት) ምስክርነት የለንም፡፡ እግዚአብሔርን ሳናውቀውም የእርሱ ነን ማለት አንችልም፡፡ ይህ ከሌለን ክርክራችን ከሰው ሳይሆን ከራሱ ከእግዚአብሔር ጋር ነው፡፡ ቃሉም ይህንን ያረጋግጥልናል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር በምድር ላይ ከሚኖሩ ጋር ክርክር አለው፡፡›› (ሆሴ. 1÷ 1)
ብዙዎች ለሃይማኖት የሚከራከሩ እንጂ ለሃይማኖት የሚመሰክሩ አይደሉም፡፡ ምስክሮች ልንሆን መጠራታችንን ቃሉ ይናገራል፡፡ ምስክር ያየና የሰማ ነው፡፡ ስለማናውቀው እግዚአብሔር እንከራከራለን፤ ስለማናውቃት ቤተ ክርስቲያን እንሟገታለን፡፡ የእኛን ማመን የምንገልጠው ሌሎችን በመስደብና በመንቀፍ ነው፡፡ ለክርስትናችን አብነት የምናደርገው ማንን ይሆን? መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከሆነ እስኪ የእርሱን ፈለግ እናስተውል እንኳን ሊሳደብ ሲሰድቡት ምላሽ አልሰጠም፡፡ እኛ ግን በአካል መሳደብ ባንችል በዘመናዊ የመገናኛ መንገድ ለመሳደብ በአደባባይ የተገለጥን ነን፡፡
በድረ-ገጻቸው የሰውን ስም እያብጠለጠሉና የስድብ ናዳ እያወረዱ በጽሑፋቸው መዝጊያ ላይ ቸር ወሬ ያሰማን¡¡¡  በማለት የሚቀልዱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቆርቋሪዎችና የክርስቶስ ወገኖች መሆናቸውን ይናገሩ እንጂ ከእነርሱ የሚወጣው የስድብ ቃል ለጆሮ የሚቀፍና የመንደር ሰዎች እስኪመስሉ ድረስ ለሕዝቡ የስድብ ዓይነት ለማስተማር እንጂ በእውነት ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የተማሩና ለአገልግሎት የተጠሩ አይመስሉም፡፡ ከዚህም ባሻገር ቤተ ክርስቲያንን በአንድ የሰንበት ት/ቤት ማደራጃና መምሪያ ሥር ባለ የጽዋ ማኅበር ለመምራት የሚያስቡ ተራራ ልብ ያላቸው ናቸው፡፡
ወገኖቼ! ከአንደበታችን የስድብና የጥላቻ እንዲሁም የሌሎችን ሕይወት የሚያብጠለጥል ቃል እያወጣን ቸር ወሬ ያሰማን¡¡¡  የሚል ምኞት ከኲርንችት በለስን ለመልቀም ከማለም የዘለቀ ልመና አይደለም፡፡ ቃሉም፡- ‹‹አትሳቱ እግዚአብሔር አይዘበትበትም፡፡ ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና›› (ገላ.6÷7) ይለናል፡፡ ከእኛ አንደበት መልካምና የበረከት ቃል ሳይወጣ ጆሮአችን መልካም ቃልን እንዲሰማ መመኘት መንፈሳዊ ቀልደኞች ያሰኘናል፡፡
ነቢዩ የሆሴዕን መጽሐፍ ምዕራፍ አራትን በሙሉ ስናነብ ላለንበት ዘመን በቂ መልዕክት ነው፡፡ የምዕራፉ አሳብ በሰፊው ቢተነተን መጽሐፍ የሚወጣው ነው፡፡ ነገር ግን ለዚህ ጽሑፍ የሚሆነንን ኃይለ-ቃል በቁጥር ስድስት ላይ ያለው ‹‹ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቷል›› የሚለው ነው፡፡ ያ ሕዝብ እውቀት ያጣ ብቻ አልነበረም እውቀትንም የሚጠላ እንደነበረ ተገልጧል፡፡ ዛሬም ብዙዎች እውቀት ከማጣት የተነሳ ብቻ የጠፉ አይደሉም፡፡ እውቀትንም የሚጠሉ ናቸው፡፡ የዚህ መገለጫውን ከዛሬው አቋማችን እንገለበጥና ነገ ደግሞ ሌላ ሰዎች ሆነን መገኘታችን ነው፡፡ የመረቅነውን እንረግማለን፣ ያጸደቅነውን እንኮንናለን፡፡ ወገኖቼ! አይደክማችሁም? እስኪ ቆም ብላችሁ አስቡ ለመጣው ነገር ሁሉ ቤተ ሙከራ መሆን ይደክማል፡፡ የዚህ ችግሩ የእግዚአብሔር ቃል እውቀት ማጣትና መጥላት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ክርክራችን ከእግዚአብሔር ጋር በመሆኑ በምንፈርድበት ይፈርድብናል፤ በምንሰፍረውም ይሰፍርልናል፡፡ ‹‹የማያስተውል ሕዝብ ይገለበጣል››፡፡
በብዙዎቻችን ሕይወት እንደሚታየው ስለማንጠየቅባቸው ሰዎች ማንነት ስናጠና፣ ስንነቅፍ፣ ስንፈርድ የእኛን ተጠያቂነት እየዘነጋን መጥተናል፡፡ ነገር ግን ሁላችንም በክርስቶስ የፍርድ ዙፋን ፊት መቆማችን የማይቀር እውነት ነው፡፡ ሐማ መርዶክዮስን ለማሰቀል የአይሁድንም ሕዝብ ለማጥፋት ሲፈጥን በፍጻሜው ራሱን በመስቀል ላይ አገኘው፡፡ ዛሬም ብዙዎችን ከቤተ ክርስቲያን ስም በመስጠትና በማባረር  የሚተጉ ወደ መስቀላቸው ፍጻሜ እየፈጠኑ መሆናቸውን የረሱ ይመስላሉ፡፡ በየአዳራሹና በየዓውደ ምሕረቱ ሕዝብን እየጠሩና የሰዎችን ስም እያብጠለጠሉ የሌሎችንም አገልግሎት እየነቀፉ ሐማ እንደ መዘነው የጥፋት ገንዘብ  እነርሱም ገንዘብ በማሰባሰብ ሥራ የተጠመዱ ወደ ፍጻሜያቸው መቃረባቸውን ቢያውቁና ንስሓ ቢገቡ መልካም ነው፡፡ ዛሬም በንስሓ ለሚመለሱ ሁሉ አምላካችን የተዘረጉ እጆችና የተከፈቱ ደጆች አሉት፡፡ ይህንን ዕድል ፈንታቸውን ካልተጠቀሙበት ግን ቃሉ እንደሚል ‹‹እውነትን በአመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በአመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቊጣ ከሰማይ ይገለጣልና›› (ሮሜ.1÷18)፡፡
ሕዝባችንም በየዐውደ ምሕረቱና የመሰብሰቢያ ቦታ ጥሪ ሲደረግለት የሚገኝ ይሁን እንጂ ለሚሰማው ቃል (ድምፅ) የሚያጣራበት ወንፊት የሌለው ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ ግን ‹‹መጽሐፍስ ምን አለ?›› በማለት የሰማውን ለመቀበልም ሆነ ለመጣል የእውነት ሚዛን ያለው ነው፡፡ ወገኖቼ! የእግዚአብሔር ቃል እውቀት ከሌለን የተባረከውን ሕዝብ ለመርገም እንደ በለዓም ስንቸኩል መንገዳችንም በፊቱ ጠማማ ሆኖ ከእግዚአብሔር ጋር እንዳንጣላ ልናስተውል ይገባል፡፡ ያለበለዚያ ‹‹የማያስተውል ሕዝብ ይገለበጣል!›› ተብሎ እንደተጻፈ የረገምነውን እንባርካለን!! እግዚአብሔር የባረከውን ሊረግም የሚችል የለምና፡፡
በመጨረሻ በሐዋርያው የቡራኬ ቃል ልሰናበት ‹‹ጌታ በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጥህ›› (2ኛ ጢሞ. 2÷7)

Wednesday, March 2, 2011

KING ( ከዲያቆን አሸናፊ)

ይቅርታ (ክፍል1)

ዘመድ አዝማድ የተወን ጓደኛ ወዳጅ ገሸሽ ያለን ሆነን ይሆናል።  በማግኘታችን የከበቡን ሰዎች ዛሬ ስናጣ ተበትነው ይሆናል።  በሐሰተኛ ምስክሮች የማይገባንን ፍርድ ተቀብለን ይሆናል።  ቅንዓታቸውን ሃይማኖትና ፍትህ አልብሰው በሚታገሉ ሰዎችም የመጠላት ቀንበር ወድቆብን ይሆናል።  የሳምናቸው ነክሰውን የቀረብናቸው ገፍትረውን አበባ የሰጠናቸው አፈር በትነውብን ወርቅ ያበደርናቸው ጠጠር መልሰውልን እህል የሰጠናቸው አፈር ሰፍረውልን ይሆናል በእኛ ምክንያት የተገኙ ሰዎች በራሳችን ላይ የሚፈነዱ የቡድን አደጋዎች ሆነውብን ይሆናል።

ፈርጅ ብዙ በሆነችው እድሜ ተለሳልሰው ገብተው በቤታችን ከተደላደሉ በኋላ በማያቋርጥ ሙግት አድክመውን ይሆናል ።  አደራ ብለን የሄድነውን ትዳራችንን ንብረታችንን ባልንጀሮቻችን ወርሰው ተቀምጠው ይሆናል።  ችግራቸው እስኪያልፍ ተጠግተውን ሲያገኙ ተረከዛቸውን አንሥተውብን ይሆናል።  አጥንት በሌለው ምላሳቸው አጥንታችንን ሰብረውት በመርዛም ቃላቸው ሕሊናችንን ጎድተው ይሆናል አልመው ቁስላችን ላይ የወረወሩት ቀስት ዛሬም እያመረቀዘ ይሆናል ለእነርሱ ክፉ እንዳልሆንን እያወቁ ከጠላት ጋር ጉድጓድ ምሰውልን ይሆናል።

በሰው ውድቀት የሚረካው ያው ሰው በሆነባት ዓለም በከሰረው ንግዳችን በፈረሰው ትዳራችን የለመጠን ተደስተው ይሆናል።  ፍቅራቸውን ነርበን ስንሄድ እንደ ረሃብተኛ እንጀራ አቅርበው ሸኝተውን ይሆናል።  ሰዎች እንደጥንቱ አልሆን ብለውን ተለዋውጠውብን ይሆናል።  ድሮ የሚያዳምጡን ሰዎች ዛሬ ቃላችን እሬት ሆኖባቸው እንደ ሸንኮራ አገዳ መጠው የጣሉን ሰዎች ሆነን ይሆናል።  ሳንፈለግ ያለልክ አክብረውን ጊዜያቸው ሲያልቅ ደግሞ ስማችንን በምናልፍበት ሁሉ አጥፍተውት ይሆናል።  ከክርስቲያን የማይጠበቅ ነገር አድርሰውብን ይሆናል።   አዎ በሆሳዕና ማግስት ስቀለው ስቀለው መባል ያሳዝናል።  እንደ አሚና (ላሊበላ) በእኛ ተዝካር ላይ ስለሚዳሩ ሰዎች ስናስብ ሕሊና ይቆስላል።  የማይዋደዱ ሰዎች እኛን ለማጥፋት ሕብረት ሲፈጥሩ ማየት ያርዳል።   መምሸቱን ሳያረጋግጡ ገና ፀሐይዋ ቆልቆል ስትል ተሰናባቹ ሲበዛ ዱዳ ያደርጋል።  ወዳጅ በገንዘብ ሲለወጥ ማየት በሕሊና ቀርቶ በገንዘብ ማሰብ ሲጀመር ከማን ጋር ነበርኩ? ያሰኛል።  ዛሬ በር ዘግተን የከተማ መናኝ መሆናችን ዝምታን መርጠን እንደማይደንቀው ፀጥ ማለታችን ሰው የማይለምድ አውሬ ነው ብለን መናገራችን ከሰው ጋር ከመኖር ከክርስቶስ ጋር በዱር መኖር ይሻላል ማለታችን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በሰው ጠባይ ተስፋ መቁረጣቸውን ለትችት አያስቸኩለንም።

በሄዱት ሰዎች እየተበሳጨን ያሉትን ማመን አቅቶን ይሆን?  አሁን ባጠገባችን ያሉት ወዳጆቻችን በእውነት የሚወዱን ልበ ልቡናችን እየነገረን ነገር ግን ከጉዳችን የተነሣ ማንንም ላለማመን ምለን ይሆን? አገር አልባ ያደረጉንን ከምንወደው ወገን የለዩንን ፍቅራችንን በአመድ ያዳፈኑትን መርሳት ቸግሮን ይሆን? ኑሮአችንን የዕንባ ያደረጉትን ለጨጓራ ለደም ብዛትና ለማድያት ያበቁንን መተው መሸነፍ መስሎን ይሆን?  እኛን የሚበላ እሳት የሚሞቁትን አይቶ እንዳላየ ማለፍ የማይሆንለት ሆኖብን ይሆን?

ውድ አንባቢ ሆይ! እናንተን የሚሰማችሁ ህመም ለዘመናት ተሰምቶኛል።  ራሴን አሸንፌ የይቅርታ ሰው ለመሆን ለብዙ ጊዜ ከራሴ ጋር ታግያለሁ።  መራራነት እጅግ ጎድቶኝ አይቻለሁ።  ስለ ይቅርታ ብዙዎች መክረውኝና ብዙ ምክር ሰምቼ መመለስ አቅቶኝ እንደነበር አስታውሳለሁ።  አንድ አባት ግን በመጨረሻ <<ለሰይጣን እንኳን ቂም በቀል የለንም አልገዛልህመ የሚል እምቢታ እንጂ ለገዛ ወንድምህ ግን ቂመኛ በመሆንህ እራስህን ልትታዘብ ይገባል ይልቁንስ ዛሬውኑ ዳንና ሂድ>> ሲሉኝ ትልቅ ቀንብር ከላዬ ወደቀ።

ከዚህ ሁሉ በላይ የይቅርታን ሕይወት ካልተለማመድን እግዚአብሔርን አባት ብሎ ለመጥራት እንደማልችል ሲገባኝ ችሎታውን እንዲሰኝ እየለመንኩ በታላቅ ንስሃ በፊቱ ወደቅሁ።  አስቀየሙኝ የምላቸው ሰዎች ስም እየጠራሁ ስጸልይላቸው ቅሬታዬ እየተቀረፈ ወደቀ።  ስናገር ይቀለኛል የሚለውን መመሪያ ጥዬ በደላቸውን ማውራት ሳቆም በዝምትአ ሃይል አገኘሁ።

ይቆየን. . .

Tuesday, March 1, 2011

KING ( ከዲያቆን አሸናፊ)

ሰውዬው መሣርያውን አስተካክሎ ሰው ሊገል በጠዋት ከቤቱ ሲወጣ ሚስቱ "ቡና ፈላ ወይ?” ብትለው “ምነው በዓርብ ምድር” ብሎ ደነገጠ ይባላል።  በአገራችን ሃይማኖት ባህል ሆኗል።  የታወቁ ሽፍቶችና ነፍሰ ገዳዮች ዳዊት ደጋሚ እንደነበሩ እንሰማለን።  በጎንደር አንድ ሽፍታ ዳዊት ሲደግም ተከታዮቹ ከፊቱ ቆመው አንድ ሰው እያለፈ ነው ምን እናድርገው? ቢሉት በመናገር ጸሎቱ እንዳየታጎል ፈርቶ እጁን በአንገቱ ላይ በመገዝገዝ ግደሉት አላቸው ይባላል።
ሕዝባችን ለእግዚአብሔር በሙሉነት መታዘዝ የመነኮሳትና የቀሳውስት ተግባር ስለሚመስለው እርሱ ያሻውን እየፈጸመ የወከላቸው ቀሳውስት እንዲተጉለት የጥምጥም በመስጠት ተረጋግቶ የተቀመጠ ነው።  ይቅርታ ባህላችን አይደለም።  ባህላችን ክስ በቀል ነው።  በገጠሩ የማያባራ ጠብ አለ እስከ ሰባት ዘር ቆጥረው ይጫረሳሉ።  ሕዝባችን ለደም እንግዳ አይደለም።  የከተማውም ሰው በሃሜት በአድመኝነት በሰው እንጀራ በመግባት . . . ተዳድፏል።  በአሁኑ ወቅት በዙ ሰው የሥጋ ጤና የአእምሮ ሰላም የለውም።  ትልቁ ችግር ግን ይቅርታ ማጣት ነው።
በአንድ ነጭ ወረቀት ላይ በብዕር አንድ ነጥብ አስቀምጠን ምን ይታያችኋል?  ብለን መቶ ሰው ብንጠይቅ ሁሉም አንድ ጥቁር ነጥብ ይታያችኋል።  ትልቅ የሆነው የወረቀቱ ንጣት ማንም አይታየውም።  አንድ ነትብ ግን ሁሉም ይታየዋል።  ስህተት በሚፈልግ ዓይን እንድንኖር የእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለም።
የታሪክና የሥነ መለኮት መጻሕፍትን ማዘጋጀት ቀላል ነው።  ድካም እንጂ ውስጣዊ ጥያቄ የለበትም።  ይቅርታን ለመጻፍ ግን ሕይወቴ ከገለባ ይልቅ እስኪቀለኝ በሚዛን ላይ ወጥቻለሁ ።  ስለዚህ ብዕሬን አስቀምጬ ራሴን ለረጅም ጊዜ አየሁት።  የእግዚአብሔር እጅ ከሌለበት ጣዕም የሌለውን እንዲህ ያለውን ሥራ ለመሥራት ለእግዚአብሔር መሸነፍን መረጥኩ የበደለልኳቸውን ሰዎች የቻልኩትን በአካል ያልቻልኩትን በደብዳቤ ይቅርታ ጠየቅሁ።  የበደሉኝ የሚመስለኝ ሰዎችም ለይቅርታ ሲደነድኑ በደሉ የእኔ ነው ብዬ እግራቸው ላይ ስወድቅ ሊገለጽ በማይቻል የፍቅር ኃይል በዕንባ ሲወድቁ አየሁ።  ለመሄድ ዳር ዳር ለሚሉት ወዳጆአህም ሁልጊዜ እንደ እንደምወዳቸው የሚገልጽ የመሸኛ ደብዳቤ ሰሰጣቸው እስከ ጊዜው በደስታ ሄዱ።
ይቅርታ ለሰዎቹ ጥቅም ከፈለኩት ይልቅ ያለ ይቅርታ በሕይወት እንደማልቆይ በተከታታይ ከገጠሙኝ በሽታዎች ተረድቻለሁ።  ችግሬ በነጻ ማፍቀር አለመቻሌ ነው።  የሰው መርህ <<ሰጥቶ መቀበል>> ነውና።  የእግዚአብሔር ስጦታ ግን <<ነጻ ስጦታ ነው>> ቢሆንም ይቅርታ የሚያደርግ እንጂ የረጋ ነገር እንዳልሆነ ስረዳ ዛሬም ወደ ይቅርታ ፍጻሜ መሄድን እናፍቃለሁ።

ይቆየን ዲ. አሸናፊ