በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
በገጠሩ የአገራችን ክፍል ሁለት በተለያየ ስፍራ የሚኖሩና ደም የተቃቡ ሰዎች ቂመኞች በመሆናቸው ሁልጊዜ በዓይነ ቁራኛ እየተጠባበቁ ነው የሚኖሩት። በአጋጣሚ እነዚህ ሁለት ጠበኞች ቤተ ከርስቲያን ለመሳለም መጥተው ከበር ላይ ከተገናኙ ወደ ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ቂምህን አውርድ በመባባል የታጠቁትን መሣሪያ ከበር ላይ አስቀምጠው ይገባሉ። ሲወጡ ደግሞ ቂምህን አንሣ ተባብለው መሣሪያቸውን አንሥተው በዓይነ ቁራኛ እየተያዩ ይለያያሉ። ለእግዚአብሔር ክብር ቢኖራቸው ግን ይቅር በተባበሉ ነበር። ቀሳውስቱም ከነቂማቸው ሲቀድሱ ግድ የላቸውም ያልበደልን ጫማ ለማስወለቅ ግን ይታገላሉ።
ጾም ጸሎት ምሕላ ማድግ የተለመደ ነው። እነዚህ በመንፈሳዊው ዓለም እንደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚቆጠሩ ናቸው። ግን ሦስት ነገሮችን ማሟላት አለባቸው። እነርሱም የጸሎት ርእስ ማየዝ እርስ በርስ ይቅር መባባልና ንስሓ መግባት ናቸው። አሊያ ዓለማ የሌለው ጾም ጸሎት ወይም ምሕላ ይሆናል ማለት ነው። ጾም ጸሎት ምሕላው ይደረጋል እንጂ በረከቱ ግን የለም። ከሚሰማ አምላክ ጋር እየተነጋገርን ለምን አልመለሰልንም? ብለን አንጠይቅም። በአገራችን ሃይማኖት ባሕል እንጂ ሕይወት አይደለምና።
የሀገራችን ሰው ችግሩን አላወቀም። እንጀራ የነሳው በሃዘን ጨለማ ያስቀመጠውን ድሪቶ ያስለበሰውን የጎረቤት ተንኮል ይመስለዋል የገዛ ሃጥያቱ መሆኑን ግን አላወቀም። ስለዚህ ምድሪቱ ፈውስ እንድታገኝ የሃዘን ማቋን እንድታወልቅ በምድሪቱ ላይ ብሔራዊ ንስሓና ይቅርታ ያስፈልጋል። ይህንን ንስሓና ይቅርታ ቤተ ክርስቲያን በተሰበረ ልብ ተቀብላ ለሕዝብና ለመንግሥት ካልገለጠች ከቤቱ የሚጀምረው የእግዚአብሔር ቁጣ ፈጥኖ ያገኛታል።
አገራችን ኢትዮጵያ የሦስት ሺህ ዓመት ታሪክ ያላት አገር ናት። በእውነቱ ስናየው ግን ሦስት ሺህ ዓመት የደም ታሪክ ነው። ሰው ሰውን ገድሎ ጀግና የሚባልበት እኔ የማክሰኞ ገዳይ እኔ የሐሙስ ገዳይ እየተባለ የሚሸለልበት ምድር ናት። እግዚአብሔርም በብዙ መንገድ ቢቀጣትም ልብ ደንዳናዋ አገር አልሰማችም።
መጦር ስትችል የሰማንያ ዓመት ሽማግሌና ከሃምሳ ዓመት በላይ የገዙ ንጉሷን ገድላለች። ጳጳሷንም ገድላ ዘፍናለች። ታላላቅ ሚኒስትሮቿን ስድሳውን በአንድ ጉድጓድ ቀብራለች። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ መሪና ጳጳስ የሚሰደድባት አገር ሆናለች። ያሉትንም ለማሳደድ የተጠማችው ምድር ራሷን አይታ ንስሓ ለመግባትና ይቅር ለመባባል ገና አልተዘጋጀችም።
የዓለም ሁሉ ትዝብት የሆነችው አገር ያለ ንስሃ ይቅርታ ከረሃብ መዝገበ ቃላት ከውድቀት ስፍራዋም አትነሳም። ማወቅ ዕዳ የሆነባት አገርና ቤተ ክርስቲያን መፍትሔአቸው ብሔራዊ ንስሓ ነው። የእግዚአብሔር እጅ ጣልቃ ባይገባ ብዙ ጊዜ ወደ ዘረኝነት ጭፍጨፋ ልናመራ የቃጣን ሕዝቦች ነን። ግን በዚሁ በከተማችን ስለሩዋንዳ የዘር እልቂት ሻማ ለኩሰን ዞረናል። ዛሬም የምናዝነው ምኞታችን ባለመፈጸሙ እንጂ እግዚአብሔርን በመግፋታችን አይደለም።
ይቅርታ እውቀት ሳይሆን መታዘዝ ነውና ይቅር ተባባሉ። አገሬንና ቤተ ክርስቲያኔንም ለይቅርታ እማፀናለሁ።
ይቆየን…ዲ.አሸናፊ
OMG NAFKOTYEE THIS SOOOOOOOO NICE YOU ARE ABSOLUTELY RIGHT LAWAKEBAT "YEKERTA IS FEKER NAW"!!!!!!
ReplyDeleteTITI