ሰውዬው መሣርያውን አስተካክሎ ሰው ሊገል በጠዋት ከቤቱ ሲወጣ ሚስቱ "ቡና ፈላ ወይ?” ብትለው “ምነው በዓርብ ምድር” ብሎ ደነገጠ ይባላል። በአገራችን ሃይማኖት ባህል ሆኗል። የታወቁ ሽፍቶችና ነፍሰ ገዳዮች ዳዊት ደጋሚ እንደነበሩ እንሰማለን። በጎንደር አንድ ሽፍታ ዳዊት ሲደግም ተከታዮቹ ከፊቱ ቆመው አንድ ሰው እያለፈ ነው ምን እናድርገው? ቢሉት በመናገር ጸሎቱ እንዳየታጎል ፈርቶ እጁን በአንገቱ ላይ በመገዝገዝ ግደሉት አላቸው ይባላል።
ሕዝባችን ለእግዚአብሔር በሙሉነት መታዘዝ የመነኮሳትና የቀሳውስት ተግባር ስለሚመስለው እርሱ ያሻውን እየፈጸመ የወከላቸው ቀሳውስት እንዲተጉለት የጥምጥም በመስጠት ተረጋግቶ የተቀመጠ ነው። ይቅርታ ባህላችን አይደለም። ባህላችን ክስ በቀል ነው። በገጠሩ የማያባራ ጠብ አለ እስከ ሰባት ዘር ቆጥረው ይጫረሳሉ። ሕዝባችን ለደም እንግዳ አይደለም። የከተማውም ሰው በሃሜት በአድመኝነት በሰው እንጀራ በመግባት . . . ተዳድፏል። በአሁኑ ወቅት በዙ ሰው የሥጋ ጤና የአእምሮ ሰላም የለውም። ትልቁ ችግር ግን ይቅርታ ማጣት ነው።
በአንድ ነጭ ወረቀት ላይ በብዕር አንድ ነጥብ አስቀምጠን ምን ይታያችኋል? ብለን መቶ ሰው ብንጠይቅ ሁሉም አንድ ጥቁር ነጥብ ይታያችኋል። ትልቅ የሆነው የወረቀቱ ንጣት ማንም አይታየውም። አንድ ነትብ ግን ሁሉም ይታየዋል። ስህተት በሚፈልግ ዓይን እንድንኖር የእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለም።
የታሪክና የሥነ መለኮት መጻሕፍትን ማዘጋጀት ቀላል ነው። ድካም እንጂ ውስጣዊ ጥያቄ የለበትም። ይቅርታን ለመጻፍ ግን ሕይወቴ ከገለባ ይልቅ እስኪቀለኝ በሚዛን ላይ ወጥቻለሁ ። ስለዚህ ብዕሬን አስቀምጬ ራሴን ለረጅም ጊዜ አየሁት። የእግዚአብሔር እጅ ከሌለበት ጣዕም የሌለውን እንዲህ ያለውን ሥራ ለመሥራት ለእግዚአብሔር መሸነፍን መረጥኩ የበደለልኳቸውን ሰዎች የቻልኩትን በአካል ያልቻልኩትን በደብዳቤ ይቅርታ ጠየቅሁ። የበደሉኝ የሚመስለኝ ሰዎችም ለይቅርታ ሲደነድኑ በደሉ የእኔ ነው ብዬ እግራቸው ላይ ስወድቅ ሊገለጽ በማይቻል የፍቅር ኃይል በዕንባ ሲወድቁ አየሁ። ለመሄድ ዳር ዳር ለሚሉት ወዳጆአህም ሁልጊዜ እንደ እንደምወዳቸው የሚገልጽ የመሸኛ ደብዳቤ ሰሰጣቸው እስከ ጊዜው በደስታ ሄዱ።
ይቅርታ ለሰዎቹ ጥቅም ከፈለኩት ይልቅ ያለ ይቅርታ በሕይወት እንደማልቆይ በተከታታይ ከገጠሙኝ በሽታዎች ተረድቻለሁ። ችግሬ በነጻ ማፍቀር አለመቻሌ ነው። የሰው መርህ <<ሰጥቶ መቀበል>> ነውና። የእግዚአብሔር ስጦታ ግን <<ነጻ ስጦታ ነው>> ቢሆንም ይቅርታ የሚያደርግ እንጂ የረጋ ነገር እንዳልሆነ ስረዳ ዛሬም ወደ ይቅርታ ፍጻሜ መሄድን እናፍቃለሁ።
ይቆየን ዲ. አሸናፊ
No comments:
Post a Comment