ይቅርታ (ክፍል1)
ዘመድ አዝማድ የተወን ጓደኛ ወዳጅ ገሸሽ ያለን ሆነን ይሆናል። በማግኘታችን የከበቡን ሰዎች ዛሬ ስናጣ ተበትነው ይሆናል። በሐሰተኛ ምስክሮች የማይገባንን ፍርድ ተቀብለን ይሆናል። ቅንዓታቸውን ሃይማኖትና ፍትህ አልብሰው በሚታገሉ ሰዎችም የመጠላት ቀንበር ወድቆብን ይሆናል። የሳምናቸው ነክሰውን የቀረብናቸው ገፍትረውን አበባ የሰጠናቸው አፈር በትነውብን ወርቅ ያበደርናቸው ጠጠር መልሰውልን እህል የሰጠናቸው አፈር ሰፍረውልን ይሆናል በእኛ ምክንያት የተገኙ ሰዎች በራሳችን ላይ የሚፈነዱ የቡድን አደጋዎች ሆነውብን ይሆናል።
ፈርጅ ብዙ በሆነችው እድሜ ተለሳልሰው ገብተው በቤታችን ከተደላደሉ በኋላ በማያቋርጥ ሙግት አድክመውን ይሆናል ። አደራ ብለን የሄድነውን ትዳራችንን ንብረታችንን ባልንጀሮቻችን ወርሰው ተቀምጠው ይሆናል። ችግራቸው እስኪያልፍ ተጠግተውን ሲያገኙ ተረከዛቸውን አንሥተውብን ይሆናል። አጥንት በሌለው ምላሳቸው አጥንታችንን ሰብረውት በመርዛም ቃላቸው ሕሊናችንን ጎድተው ይሆናል አልመው ቁስላችን ላይ የወረወሩት ቀስት ዛሬም እያመረቀዘ ይሆናል ለእነርሱ ክፉ እንዳልሆንን እያወቁ ከጠላት ጋር ጉድጓድ ምሰውልን ይሆናል።
በሰው ውድቀት የሚረካው ያው ሰው በሆነባት ዓለም በከሰረው ንግዳችን በፈረሰው ትዳራችን የለመጠን ተደስተው ይሆናል። ፍቅራቸውን ነርበን ስንሄድ እንደ ረሃብተኛ እንጀራ አቅርበው ሸኝተውን ይሆናል። ሰዎች እንደጥንቱ አልሆን ብለውን ተለዋውጠውብን ይሆናል። ድሮ የሚያዳምጡን ሰዎች ዛሬ ቃላችን እሬት ሆኖባቸው እንደ ሸንኮራ አገዳ መጠው የጣሉን ሰዎች ሆነን ይሆናል። ሳንፈለግ ያለልክ አክብረውን ጊዜያቸው ሲያልቅ ደግሞ ስማችንን በምናልፍበት ሁሉ አጥፍተውት ይሆናል። ከክርስቲያን የማይጠበቅ ነገር አድርሰውብን ይሆናል። አዎ በሆሳዕና ማግስት ስቀለው ስቀለው መባል ያሳዝናል። እንደ አሚና (ላሊበላ) በእኛ ተዝካር ላይ ስለሚዳሩ ሰዎች ስናስብ ሕሊና ይቆስላል። የማይዋደዱ ሰዎች እኛን ለማጥፋት ሕብረት ሲፈጥሩ ማየት ያርዳል። መምሸቱን ሳያረጋግጡ ገና ፀሐይዋ ቆልቆል ስትል ተሰናባቹ ሲበዛ ዱዳ ያደርጋል። ወዳጅ በገንዘብ ሲለወጥ ማየት በሕሊና ቀርቶ በገንዘብ ማሰብ ሲጀመር ከማን ጋር ነበርኩ? ያሰኛል። ዛሬ በር ዘግተን የከተማ መናኝ መሆናችን ዝምታን መርጠን እንደማይደንቀው ፀጥ ማለታችን ሰው የማይለምድ አውሬ ነው ብለን መናገራችን ከሰው ጋር ከመኖር ከክርስቶስ ጋር በዱር መኖር ይሻላል ማለታችን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በሰው ጠባይ ተስፋ መቁረጣቸውን ለትችት አያስቸኩለንም።
በሄዱት ሰዎች እየተበሳጨን ያሉትን ማመን አቅቶን ይሆን? አሁን ባጠገባችን ያሉት ወዳጆቻችን በእውነት የሚወዱን ልበ ልቡናችን እየነገረን ነገር ግን ከጉዳችን የተነሣ ማንንም ላለማመን ምለን ይሆን? አገር አልባ ያደረጉንን ከምንወደው ወገን የለዩንን ፍቅራችንን በአመድ ያዳፈኑትን መርሳት ቸግሮን ይሆን? ኑሮአችንን የዕንባ ያደረጉትን ለጨጓራ ለደም ብዛትና ለማድያት ያበቁንን መተው መሸነፍ መስሎን ይሆን? እኛን የሚበላ እሳት የሚሞቁትን አይቶ እንዳላየ ማለፍ የማይሆንለት ሆኖብን ይሆን?
ውድ አንባቢ ሆይ! እናንተን የሚሰማችሁ ህመም ለዘመናት ተሰምቶኛል። ራሴን አሸንፌ የይቅርታ ሰው ለመሆን ለብዙ ጊዜ ከራሴ ጋር ታግያለሁ። መራራነት እጅግ ጎድቶኝ አይቻለሁ። ስለ ይቅርታ ብዙዎች መክረውኝና ብዙ ምክር ሰምቼ መመለስ አቅቶኝ እንደነበር አስታውሳለሁ። አንድ አባት ግን በመጨረሻ <<ለሰይጣን እንኳን ቂም በቀል የለንም አልገዛልህመ የሚል እምቢታ እንጂ ለገዛ ወንድምህ ግን ቂመኛ በመሆንህ እራስህን ልትታዘብ ይገባል ይልቁንስ ዛሬውኑ ዳንና ሂድ>> ሲሉኝ ትልቅ ቀንብር ከላዬ ወደቀ።
ከዚህ ሁሉ በላይ የይቅርታን ሕይወት ካልተለማመድን እግዚአብሔርን አባት ብሎ ለመጥራት እንደማልችል ሲገባኝ ችሎታውን እንዲሰኝ እየለመንኩ በታላቅ ንስሃ በፊቱ ወደቅሁ። አስቀየሙኝ የምላቸው ሰዎች ስም እየጠራሁ ስጸልይላቸው ቅሬታዬ እየተቀረፈ ወደቀ። ስናገር ይቀለኛል የሚለውን መመሪያ ጥዬ በደላቸውን ማውራት ሳቆም በዝምትአ ሃይል አገኘሁ።
ይቆየን. . .
በእውነት ይቅርታ ታላቅ ነው!ድንቅ የሆነ መልዕክት አዘል ትምህርት ነው እናመሰግናለን ዲ/አሸናፊ
ReplyDeletekeyekerta belaye mn yenore yehone. As a human I find myself very vulnerable. Even after we have done our yekerta we still have the trace of that bad feeling. I wonder if that will ever go away. And also are we really saying yekerta cause we really feel sincerely bad about what we did or what we have done or are we saying it to make peace with that person. There is a lot of us who still keep doing the same thing even after we ask or give the forgiveness.
ReplyDelete