<<የማያስተውል ሕዝብ ይገለበጣል>>
ሁላችንም እንደምናውቀው የመገልበጥ አደጋ እጅግ ትልቅ ጉዳት ያለው ነው፡፡ በዓለማችን ላይ በዚህ አደጋ ምክንያት ብዙ ጉዳቶችን አይተናል፡፡ በአገራችንም የወቅቱ አሳሳቢ ጉዳይ በተሽከርካሪ አማካይነት የሚደርሰው የግጭትና የመገልበጥ አደጋ ነው፡፡
ሕይወት ሲጠፋ፣ ንብረት ሲወድም፣ አካል ጉዳተኝነት ሲጨምር ማየትና መስማት የጆሮአችን ቀለብ ከሆነ ሰንብቷል፡፡ ይህ አደጋም የሚከሰተው ማስተዋል በጎደላቸው አሽከርካሪዎች ምክንያት መሆኑ ግልጽና የሚታወቅ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በአገራችን ተሽከርካሪን መጠቀም ትልቅ ሥጋት እየፈጠረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ መንግሥትም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ እርምጃዎችን ቢወስድም የሕግ አንቀጾች ቢረቀቁም አደጋው ግን በቊጥር ይቀንስ እንጂ ሥጋቱ አልቀረም፡፡
የዚህ አደጋ ትልቁ መንስኤ የማያስተውሉ አሽከርካሪዎች መብዛታቸው ነው፡፡ እንግዲህ አለማስተዋል ለመገልበጥ አደጋ ይዳርጋል፡፡ መፍትሔውም ማስተዋል ብቻ ነው፡፡ ውድ ሕይወትን እንዲሁም ዋጋ ያለው ንብረትን ለከፋ አደጋ ላለመዳረግ ማስዋል ትልቁ ቁልፍ ነው፡፡
ነቢዩ ‹‹የማያስተውል ሕዝብ ይገለበጣል›› በማለት ይናገራል፡፡ ለካስ ወገኖች! በመንፈሳዊውም ዓለም ትልቅ የመገልበጥ አደጋ አለ፡፡ ይህ አደጋም የሚከሰተው እንዲሁ ባለማስተዋል ነው፡፡ ነቢዩ ይህንን በተናገረበት ምዕራፍ ላይ የእስራኤል ሕዝብ ስለነበረበት መንፈሳዊ ውድቀት አስቀድሞ በመግለጥ ነው፡፡ ምዕራፉ ሲጀምር እንዲህ ይላል፡ - ‹‹ እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፡- እውነትና ምሕረት እግዚአብሔርን ማወቅ በምድር ስለሌለ እግዚአብሔር በምድር ላይ ከሚኖሩ ጋር ክርክር አለው፡፡›› (ሆሴ. 1÷ 1)
ለዚያ ሕዝብ መገልበጥ ምክንያት እውነትና ምሕረት እግዚአብሔርም ማወቅ አለመኖሩ ነው፡፡ ከእውነት ይልቅ ለሐሰትና ለስህተት ከምሕረት ይልቅ ለፍርድና ለነቀፋ እግዚአብሔርን ከማወቅ ይልቅ ስለሰዎች ለማወቅ የሚኖር ሕዝብ ትልቅ የመገልበጥ አደጋ እንደሚደርስበት ቃሉ ያረጋግጣል፡፡ የክርስትናው መሠረት እውነትና ምሕረት እንዲሁም እግዚአብሔርን ማወቅ ነው፡፡
እውነት፡ - የአምልኮ መሠረት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ 4 ÷ 24 ላይ እንደተናገረው እግዚአብሔርን ማምለክ በእውነትና በመንፈስ ነው፡፡ ሕዝብንም አርነት የሚያወጣው እውነት ነው፡፡ ቃሉም ‹‹እውነት አርነት ያወጣችኋል›› (ዮሐ. 8÷32) ይላል፡፡ እግዚአብሔርን በልማድ፣ በሥርዓትና በስሜት ለማምለክ የምናስብ ከሆነ ክርክራችን ከእግዚአብሔር ነው፡፡ ልማዳችንም ሆነ ሥርዓታችን ፋይዳ የሚኖረው አምልኮአችን እውነት ላይ ሲመሠረት ነው፡፡ ያለበለዚያ በአሸዋ ላይ እንደተመሠረተው ቤት የወሬ ንፋስና የመከራ ወጀብ በመጣ ጊዜ ቤቱ አደጋ ላይ መውደቁ አይቀርም፡፡
ምሕረት፡- ከእግዚአብሔር ባሕርይ አንዱ ምሕረት ነው፡፡ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለው መልካምነት ነው፡፡ መጽሐፉ እንደሚነግረን እርሱ ለክፉዎችና ለመልካሞች ፀሐይንና ዝናብን ያለ ልዩነት ይሰጣል፡፡ እኛ ብንሆን ግን ለጠላነውና ለወደድነው በፈረቃ እናከፋፍል ነበር፡፡ ከእርሱ የምንማረው ግን ለምንጠላቸው እንኳ መልካምነት እንደሚገባ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ግን የሚወዱንን እንኳ መውደድ እያቃተን ነው፡፡
እግዚአብሔርን ማወቅ፡- እግዚአብሔርን ማወቅ የክርስትናው ዐቢይ ነገር ነው፡፡ የማናውቀውን አምላክ እንዴት ልናመልክ እንችላለን? ብዙዎች ግን ሳያውቁት ያመልኩታል፡፡ ጳውሎስ በአቴና ሳለ የአቴና ሰዎች ሳያውቁት መሠዊያ ሠርተው የሚያመልኩት አምላክ እንደነበራቸው አየና የማያውቁትን አምላክ ማምለክ ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ ብቸኛውን አምላክ አስተዋወቃቸው፡፡ ዛሬም ብዙዎች ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አያውቁትም ግን በስሙ ይጠራሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያንን አያውቋትም ግን ስለእርሷ ይሟገታሉ፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች ለመሆናቸውም የሕይወት ምስክርነት የሌላቸው ናቸው፡፡ ወገኖቼ! ይህ ቃል እኛን ኦርቶዶክሳውያንን ይመለከታል፡፡ የአብዛኛው ሕዝባችን መንፈሳዊ ሕይወት በእነዚህ መሠረቶች ላይ የቆመ አይደለም፡፡ ሆሳዕና! ብሎ ለማመስገን የሚቸኩል ዳግመኛም ስቀለው! ለማለት የማይዘገይ እንደ ውሃ በቀደዱለት ቦይ የሚፈስ ነው፡፡ ነገር ግን ወገኖቼ! ለማመስገንም ለመርገምም አንቸኩል፡፡ የምንሰማውንና የምናየውን በማስተዋል እንመርምር፡፡ ቃሉ ‹‹የማያስተውል ሕዝብ ይገለበጣል›› ይላልና፡፡
የእስራኤል ሕዝብ የተነቀፈው መሠረታዊ የእምነት መገለጫውን በማጣቱ ነው፡፡ ያለ እውነት ልናመልክ አንችልም፡፡ ያለ ምሕረት (በጎነት) ምስክርነት የለንም፡፡ እግዚአብሔርን ሳናውቀውም የእርሱ ነን ማለት አንችልም፡፡ ይህ ከሌለን ክርክራችን ከሰው ሳይሆን ከራሱ ከእግዚአብሔር ጋር ነው፡፡ ቃሉም ይህንን ያረጋግጥልናል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር በምድር ላይ ከሚኖሩ ጋር ክርክር አለው፡፡›› (ሆሴ. 1÷ 1)
ብዙዎች ለሃይማኖት የሚከራከሩ እንጂ ለሃይማኖት የሚመሰክሩ አይደሉም፡፡ ምስክሮች ልንሆን መጠራታችንን ቃሉ ይናገራል፡፡ ምስክር ያየና የሰማ ነው፡፡ ስለማናውቀው እግዚአብሔር እንከራከራለን፤ ስለማናውቃት ቤተ ክርስቲያን እንሟገታለን፡፡ የእኛን ማመን የምንገልጠው ሌሎችን በመስደብና በመንቀፍ ነው፡፡ ለክርስትናችን አብነት የምናደርገው ማንን ይሆን? መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከሆነ እስኪ የእርሱን ፈለግ እናስተውል እንኳን ሊሳደብ ሲሰድቡት ምላሽ አልሰጠም፡፡ እኛ ግን በአካል መሳደብ ባንችል በዘመናዊ የመገናኛ መንገድ ለመሳደብ በአደባባይ የተገለጥን ነን፡፡
በድረ-ገጻቸው የሰውን ስም እያብጠለጠሉና የስድብ ናዳ እያወረዱ በጽሑፋቸው መዝጊያ ላይ ቸር ወሬ ያሰማን¡¡¡ በማለት የሚቀልዱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቆርቋሪዎችና የክርስቶስ ወገኖች መሆናቸውን ይናገሩ እንጂ ከእነርሱ የሚወጣው የስድብ ቃል ለጆሮ የሚቀፍና የመንደር ሰዎች እስኪመስሉ ድረስ ለሕዝቡ የስድብ ዓይነት ለማስተማር እንጂ በእውነት ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የተማሩና ለአገልግሎት የተጠሩ አይመስሉም፡፡ ከዚህም ባሻገር ቤተ ክርስቲያንን በአንድ የሰንበት ት/ቤት ማደራጃና መምሪያ ሥር ባለ የጽዋ ማኅበር ለመምራት የሚያስቡ ተራራ ልብ ያላቸው ናቸው፡፡
ወገኖቼ! ከአንደበታችን የስድብና የጥላቻ እንዲሁም የሌሎችን ሕይወት የሚያብጠለጥል ቃል እያወጣን ቸር ወሬ ያሰማን¡¡¡ የሚል ምኞት ከኲርንችት በለስን ለመልቀም ከማለም የዘለቀ ልመና አይደለም፡፡ ቃሉም፡- ‹‹አትሳቱ እግዚአብሔር አይዘበትበትም፡፡ ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና›› (ገላ.6÷7) ይለናል፡፡ ከእኛ አንደበት መልካምና የበረከት ቃል ሳይወጣ ጆሮአችን መልካም ቃልን እንዲሰማ መመኘት መንፈሳዊ ቀልደኞች ያሰኘናል፡፡
ነቢዩ የሆሴዕን መጽሐፍ ምዕራፍ አራትን በሙሉ ስናነብ ላለንበት ዘመን በቂ መልዕክት ነው፡፡ የምዕራፉ አሳብ በሰፊው ቢተነተን መጽሐፍ የሚወጣው ነው፡፡ ነገር ግን ለዚህ ጽሑፍ የሚሆነንን ኃይለ-ቃል በቁጥር ስድስት ላይ ያለው ‹‹ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቷል›› የሚለው ነው፡፡ ያ ሕዝብ እውቀት ያጣ ብቻ አልነበረም እውቀትንም የሚጠላ እንደነበረ ተገልጧል፡፡ ዛሬም ብዙዎች እውቀት ከማጣት የተነሳ ብቻ የጠፉ አይደሉም፡፡ እውቀትንም የሚጠሉ ናቸው፡፡ የዚህ መገለጫውን ከዛሬው አቋማችን እንገለበጥና ነገ ደግሞ ሌላ ሰዎች ሆነን መገኘታችን ነው፡፡ የመረቅነውን እንረግማለን፣ ያጸደቅነውን እንኮንናለን፡፡ ወገኖቼ! አይደክማችሁም? እስኪ ቆም ብላችሁ አስቡ ለመጣው ነገር ሁሉ ቤተ ሙከራ መሆን ይደክማል፡፡ የዚህ ችግሩ የእግዚአብሔር ቃል እውቀት ማጣትና መጥላት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ክርክራችን ከእግዚአብሔር ጋር በመሆኑ በምንፈርድበት ይፈርድብናል፤ በምንሰፍረውም ይሰፍርልናል፡፡ ‹‹የማያስተውል ሕዝብ ይገለበጣል››፡፡
በብዙዎቻችን ሕይወት እንደሚታየው ስለማንጠየቅባቸው ሰዎች ማንነት ስናጠና፣ ስንነቅፍ፣ ስንፈርድ የእኛን ተጠያቂነት እየዘነጋን መጥተናል፡፡ ነገር ግን ሁላችንም በክርስቶስ የፍርድ ዙፋን ፊት መቆማችን የማይቀር እውነት ነው፡፡ ሐማ መርዶክዮስን ለማሰቀል የአይሁድንም ሕዝብ ለማጥፋት ሲፈጥን በፍጻሜው ራሱን በመስቀል ላይ አገኘው፡፡ ዛሬም ብዙዎችን ከቤተ ክርስቲያን ስም በመስጠትና በማባረር የሚተጉ ወደ መስቀላቸው ፍጻሜ እየፈጠኑ መሆናቸውን የረሱ ይመስላሉ፡፡ በየአዳራሹና በየዓውደ ምሕረቱ ሕዝብን እየጠሩና የሰዎችን ስም እያብጠለጠሉ የሌሎችንም አገልግሎት እየነቀፉ ሐማ እንደ መዘነው የጥፋት ገንዘብ እነርሱም ገንዘብ በማሰባሰብ ሥራ የተጠመዱ ወደ ፍጻሜያቸው መቃረባቸውን ቢያውቁና ንስሓ ቢገቡ መልካም ነው፡፡ ዛሬም በንስሓ ለሚመለሱ ሁሉ አምላካችን የተዘረጉ እጆችና የተከፈቱ ደጆች አሉት፡፡ ይህንን ዕድል ፈንታቸውን ካልተጠቀሙበት ግን ቃሉ እንደሚል ‹‹እውነትን በአመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በአመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቊጣ ከሰማይ ይገለጣልና›› (ሮሜ.1÷18)፡፡
ሕዝባችንም በየዐውደ ምሕረቱና የመሰብሰቢያ ቦታ ጥሪ ሲደረግለት የሚገኝ ይሁን እንጂ ለሚሰማው ቃል (ድምፅ) የሚያጣራበት ወንፊት የሌለው ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ ግን ‹‹መጽሐፍስ ምን አለ?›› በማለት የሰማውን ለመቀበልም ሆነ ለመጣል የእውነት ሚዛን ያለው ነው፡፡ ወገኖቼ! የእግዚአብሔር ቃል እውቀት ከሌለን የተባረከውን ሕዝብ ለመርገም እንደ በለዓም ስንቸኩል መንገዳችንም በፊቱ ጠማማ ሆኖ ከእግዚአብሔር ጋር እንዳንጣላ ልናስተውል ይገባል፡፡ ያለበለዚያ ‹‹የማያስተውል ሕዝብ ይገለበጣል!›› ተብሎ እንደተጻፈ የረገምነውን እንባርካለን!! እግዚአብሔር የባረከውን ሊረግም የሚችል የለምና፡፡
በመጨረሻ በሐዋርያው የቡራኬ ቃል ልሰናበት ‹‹ጌታ በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጥህ›› (2ኛ ጢሞ. 2÷7)
No comments:
Post a Comment