እኛም አውቀናል …! ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
ለተከበራችሁ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ለምትገኙ ሴቶችም ወንዶችም ኢትዮጵያውያን!!በዛሬው ዕለት እጅግ አጠር ባለ መልኩ የዓባይን ጉዳይ በተመለከተ ማናችንም ብንሆን ልንስተው የማይገባ እውነት ላወሳችሁ እወዳለሁ። ይኸውም ኢትዮጵያዊ ሆኖ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን ካለበት የደከረተና የከረፋ የባርነት፣ የውርደት፣ የሰደት፣ የረሀብ፣ የጉስቁልና እንዲሁም ከማያባራ የቅሶና የዋይታ ኑሮ ወጥቶ የሰላምና የዕረፍት ሕይወት ይመራ ዘንድ የሚጠላ፤ የኢትዮጵያ ምድር ትንሣኤ የማይዋጥለትና እንደ ኮሶ መድኃኒት የሚከነክነው ፍጥረት አይኖርም! ሊኖርም አይችልም። ሀገራችን ኢትዮጵያ ከ80% በላይ ባለቤት የሆነውን ፈሳሽ ተገድቦ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተጠቃሚ ቢሆንና ለውጥ በምድራችንና ብልጽግና በኢትዮጵያ ሕዝብ ቢመጡ የማይዋጥለት ሌላ ማንም ሳይሆን የኢህአዴግ መንግሥት ራሱ ብቻ ነው።
የዚህ ያለ ሕዝብ ይሁንታ በጠመንጃ በሥልጣን ላይ የሚገኘውን መንግሥት የሚደንቅና የሚያሳዝነው ደንባራ ገጽታ አንዱ የተመለከትን እንደሆነ እነሱ ብቻ አዋቂዎች፣ ብልጦች፣ የሚያስቡትንና የሚመክሩትን የላቀና የማይደረስበት ራሳቸውን ከሰው በላይ አድገው ሲወስዱና ሲቆጥሩ በአንጻሩ ደግሞ ሰፊውን ሕዝብ ምንም የማያውቅ የአብርሃም በግ አድርገው መፈረጃቸው ነው። ይሁንና ዛሬ ማለት ትናንት ሊሆን እንደማይችል ከሰው ልጅ በላይ ነፋሳት ምስክርነታቸው አሰምተዋል።
ዓባይ ተገድቦ ለኢትዮጵያ ምድርና ሕዝብ ረብ ይዋል ሲባል የሁላችን ሀገር ወዳድ ዜጎች የላቀ ደስታ ነው። በዚህ ግልጥ ባለ ሀሳብ ላይ አንዱ ከሻሽ ሌላው ተከሳሽ ወይንም ደግሞ አንዱ የጭዋ ሌላው ደግሞ የባርያዋ ልጅ ተብሎ ነገር አይኖርም። ጥያቄው ከሊቅ እስከ ደቂቅ የተቀጣጠለውን እሳት በውስጡ አምቆ ይዞ የማይበጀውና የማይፈልገውን ከትክሻው አሽንቀጥሮ ለመጣል ለለውጥ በለውጥ ትርክ ላይ ለመሮጥ በተጠንቀቅ በቆመበት ሰዓት (በቃ! ለማለት ነው) ዓባይ ዓባይ ማልትስ እኛም አውቀናል … አይስብልም ወይ ጉበዝ? አሁንስ እነዚህ ሰፈርተኞች በማን ደምና ነፍስ ዘመነ ሥልጣናቸውን ያራዝሙ?
እንግዲህ ምን እንላለን በድጥ ላይ የቆማችሁ ሞኞችና ቅሎች ሳላችሁ ተራ ተንኮልና ሴረኝነት እውቀትና ጥበብ ሆኖ ከተሰማችሁና ከመሰላችሁ ዓባይ በማለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ ለመስለብ፣ ከገባችሁበት ጉድጓድ ለመውጣት እንደ መሰላል ለመጠቀምና የላላችውን ፈትል ዳግም ለመለቀብ ከሆነ ዓባይ እንደ ባድመ ለተጨማሪ አስር ዓመታት በግርግር የሚያሰነብታችሁ ሳይሆን ስትበቅሉ ጀምሮ እስከ ዛሬው ዕለት የዘራችሁትን ዘር የሚያሳጭዳችሁ ማዕበል ለመሆኑ አትዘንጉ።
በመጨረሻ መንግሥታት ሕዝብን አንድ ሁለት ጊዜ ያታልሉ ይሆናል በሦስተኛው ግን ተራው የሕዝቡ ይሆንና አንድና ሁለት በሌለው ሁኔታ ጭራሽ ለዘልአለም እንደሚሽራቸውና እንደሚቀብራቸው ሳይታለም የተፈታና ፀሐይ ያሞቀው የአደባባይ ምሥጢር ከመሆኑ ባሻገር በተጨማሪ በአንድም በሌላም ምክንያት ያለ እውቀት ከጀርባው ሞት ባለበት አጀንዳ ለተሰለፍን ዜጎች የምለው ነገር ቢኖር እውነት የኢህአዴግ መንግሥት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመጥቀም ሳይሆን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ፍርድ ለማምለጣና ጠፍተህ ለማጥፋት የጠነሰሰው ሴራ መሆኑ ተገንዝበን በምንም ዓይነት መልኩ ከጥቅሙ ይልቅ ኪሳራው በሚያመዝነው አጀንዳ ላይ ገብተን የታራክ ተወቃሾች ከመሆን ለመትረፍ ራሳችንን ማንኛውም ዓይነት ድጋፍ ከመስጠት በመቆጠብ ዜግነታዊ ግዴታችንን እንወጣ ዘንድ ጥሬን አቀርባለሁ።
ሀገር ነጻ ስትወጣ በግርግር ሳይሆን በሥራ የሀገራችን እና የሕዝባችን ታሪክ እንለውጣለን!!
ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል