የምድሪቱ ጉዞና የማንቂያው ደወል ድምፅ
(ጌዲዮን)
"ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላዕክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም "(ማቴ 24፡ 36)
" በመሸ ጊዜ ሰማይ ቀልቷልና ብራ ይሆናል ትላላችሁ፡፡የሰማዩን ፊትማ መለየት ታውቃላችሁ የዘመኑንስ ምልክት መለየት አትችሉምን?" (ማቴ 16፡3)
"ምሳሌዋንም ከበለስ ተማሩ ጫፏ ሲለሰልስ ቅጠሏም ሲያቆጠቁጥ ያን ጊዜም በጋ እንደቀረበ ታውቃላችሁ፡፡" (ማቴ 24፣32)
የዘመንን ፊት ስለመለየት ወይም "ስለዚያች ቀንና ሰለዚያች ሰዓት" ሰለተባለው ድንገተኛ ክስተት ለማወቅ የተለየ ወርክ ሾፕ እና ሲምፖዚየም ማዘጋጀት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ቤተ ሙከራ ማካሄድ በብዙ ሚሊዮን ሰልፈኛ አደራጅቶ በአደባባይ አመፅ መቀስቀስ አልፎም የአርባ ቀን ጾም ፀሎት መያዝ ላይጠበቅብን ይችላል፡፡ የዘመኑን ፊት ማን እንዲህ በቀላሉ ይለያል? የሚገርመው ትውልድ እንዲህ በሰለጠነበት እና ዘመን እንዲህ በረቀቀበት የመሬታችን ጉዞ ውስጥ ለአንድ ጊዜ የሚሆን የሰው ልጅ ከተነገረላት በለስ ተምሮ የበጋን መቅረብ ከመገመትና ከመተንበይ ባለፈ ለበጋና ለክረምት መፈራረቅ ከመሬት ዑደትና ከተፈጥሮ ክስተት በቀር እግዚአብሔር ስለሚባለው የነገሮች ሁሉ መጀመሪያና ፣ መጨረሻ የክስተቶች ሁሉ ማጠንጠኛ ማሰብ ቆም ብሎም መጠየቅ አይፈልግም፡፡ ያመዋል ምን አልባትም ይህን የማድረግ የህይወት አቅጣጫው አሁን ካለበት ሁኔታ 360 ዲግሪ ዞሮ ህይወትን ሌላኛዋ መልክ እንዲያጠና ስለሚገደድ ይፈራል፡፡ የሚፈልገው በደመ ነፍስ መኖር ነው፡፡ በመብላት፣ በመጠጣት፣ ልዮ ፋሽን በማሳደድ ፣ ቪላ በመገንባት፣ ቆንጆ ሴቶች (ወንዶች) በመምረጥ፣ የተሻለ የስራ ቦታ በማመቻቸት፣ ተሰሚነት በሚያስገኙ መድረኮች አስገራሚ ዲስኩሮችን በማሰማትና ምድሪቱን በአሸናፊነትና በለውጥ ማማ ላይ ማስቀመጥ ነው፡፡
እኛ እኮ ጉዶች ነን፡፡ እጅግ የበዛን የበዛብን ጉዶች ሁሌም የህይወትን አንድ መልክ ብቻ የምንመዝን፡፡ ለሰው፣ ለትውልድ፣ ለህዝብ ፣ ለአለም ዲሞክራሲን ስንሰጥ ዲሞክራሲን ስንሰብክ ፣ በራሳችን ላይ የጨከንን አምባገነኖች ነን፡፡ ነፍሳችን በነፃነት እንዳታስብ ፣ ህሊናችን የሚያምንበትን እንዳናራምድ እውነትን በእውቀት የገደልን እና መልስ ለሚሹ የውስጥ ጩህትና ኡኡታችን የበዛን የበዛብን ቢሮክራቶች እና እንዴት ለራሳችን ዴሞክራሲን እንስበክ ? ይልቁኑ "ይህ ልጃችን እንደሆነ እውርም ሆኖ እንደተወለደ እናውቃለን፡፡ዳሩ ግን አሁን እንዴት እንዳየ አናውቅም ወይንም ዓይኖቹን ማን እንደከፈተ እኛ አናውቅም ጠየቁት እርሱ ሙሉ ሰው ነው እርሱ ስለራሱ ይናገራል " ማለት ይቀለናል ቀላሉ የማምለጫ መንገድ ይሔ ነንውና ታዲያ ለነፍሳችን ምን ዲሞክራሲ ያስፈልጋታል? ምክንያቱም
"አይሁድን ስለፈሩ ይህን አሉ" ለምን ይህን አሉ? እነሱ ከዘመኑ ፊት ይልቅ ፍርሃታቸው የሰው ፊት ነበርና ይህን አሉ፡፡ ይህን በማለትም ማህበራዊ ኑሮን ፣ እድርና እቁብን፣ ሰርግ ፣መልስ፣ ቅልቅልን፣ ገናና ፋሲካን በፍቅር በህብር በፌሽታ ያሳልፋሉ፡፡ ይህ ባይሆን ደግሞ "እርሱ ክርስቶስ ነው ብሎ የሚመሰክር ቢኖር ከምኩራብ እንዲያወጡት አይሁድ ከዚህ በፊት ተስማምተው ነበርና" (ዮሐ 9፡18-23) ስለተባለ የክህደት አድማ በአዋጅ ተለፈፈ፡፡ ሰው ለነፃነትና ለዲሞክራሲ አደባባይ ይወጣል ድምፁን ያሰማል እዚህ በተቃራኒው መንፈሳዊ ዲሞክራሲን መንፈሳዊ አርነትን ለመግደል፣ ለክህደትና ለእውነት ሞትና ስቃይን ለመጋበዝ ትውልድ ባንድ ተስማምቶ ሰልፍ ይወጣል ፡፡ ታዲያ ይህ ወገን የሰማይን ፊት እንጂ የዘመኑን ፊት እንዴት ይለያል? የዘመኑን ፊት በጽድቅ፣ በንጽህና፣ በታማኝነት፣ በትጋት፣ በእውቀት፣ በጭምትነት፣ ራስን በመግዛት ለህሊና በመታመን፣ ለእውነት በመኖርና በመሞት ከሁሉ በላይ ደግሞ በእምነት በመኖር የሚገኝ ነው፡፡ የሚገለጥ ነው፡፡ አሁን ማን ይሙት(እንበልና እንደተራቾቻችን) የዚህን ዘመን ፈተናና ስቃይ ልብ ብሎ ለሚመረምር "ያን ጊዜ በጋ እንደቀረበ ታውቃላችሁ" እንደተባለላት በለስ ጌታችሁ በደጅ እንደቀረበ እወቁ፡፡ ማለትም ከግንዛቤ ማስወጣት ይኖርብን ይሆን ወይስ "ስምንተኛው ሺ ቀርቧል" እየተባለ የፌዝ ማጣፈጫ የሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጻአት ለኛ ከቁም ነገር የሚጻፍ አልሆነብን ይሆን ? እኔ ግን የምድሪቷ ጉዞና የደውል ድምጽ በለሆሳስ እያስተጋባ እንደሆነ አስባለሁ፡፡ የሚያስደነግጠኝ ግን ነገሩ ሁሉ ልክ እንደ ኖህ፣ እንደ ሎጥ ዘመን ታሪክ "የአስረሽ ምችው ዘመን ታሪክ" አንዳይደግም ነው፡፡
"ሊበሉ ሊጠጡ ተቀመጡ ሊዘፈኑ ተነሱ" አይነት
ፍቅር ሲቀዘቅዝ፣ ወንድም ወንድሙን ሊያጠፋ ሲነሳ ስጋ ሁሉ ለራሱ ነፍስ ብቻ ሲጠበብና ሲጨነቅ፣ ወላጅ በአደባባይ ሲዋረድ፣ የቤተክርስቲያን ክብር በስጋዊያንና በአለማውያን ልክ የለሽ ምኞት ሲገሰስ፣ ጽድቅ፣ ቅድስና፣ ቅንነት፣ ታማኝነት፣ ራስን መግዛት፣ በጎነትና ንፁህ አምልኮ . . . . የሞኞች ስብከት ሆነው ሲተረኩ እንዴትስ የዘመኑ መልክ ለትውልዱ ጠፍቶታል፡፡ ለማለት እንገደድ ይሆን? ጭንቁ የሚጀምረውም እዚህ ላይ ነው፡፡ አልያም ደግሞ ግድ ከሆነብን እንደ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሀን ወቅታዊ ክስተቶችን እየተከታተልን ለምዕመኖቻችን ማሳወቅ ግድ ሊለን ነው፡፡ ዕምነት ያልከፈተው አይን ጋዜጣና፣ ቴሌቭዥን ወይም የቴክኖሎጂው "በረከት" የዲሽ አገልግሎት በምድራችንና በዘመናችን መካከል ላይ የሚፈፀመውን ጉድ እቤታችን ድረስ ስበው ስለሚያመጡልን "ወይ ጉድ" እያልን እየተደመምን እጃችንን በአፋችን ላይ እያኖርን ቀኖቻችንን እንገፋለን፡፡ ንቁና ብልህ የዕምነት ሰው ግን ከመጽሐፍም ከዘመንም እየተማረ ለእግዚአብሔር እውነት ይገዛል፡፡ አሁንም ንቁና ብልህ ሰው ከዘመኑ ፊት እየተማረ ከዓለም ጋር ያለውን ቁርኝት አቋርጦ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ጽኑ ህብረት ይበልጡኑ ያጠናክራል፡፡
ü ህዝብ በህዝብ ላይ ሲነሳ እያየን
ü የምድር መናወጥ የሬክታር መጠኑን እየለካን
ü ጎርፍና የነፋስ ጉልበትን እየመዘንን
ü የፍቅር መቀዝቀዝና የጥላቻ መጠንን መበርከቱን እየቃኘን
ü ጦርነትን ጦርንና የጦር ወሬን እያደመጥን
"ወይ ስምንተኛው ሺህ" እያልን እየተረትን እምናልፍ ከሆነ በዕርግጥም የእውነት መስመሩን ስተናልና ቆም ብለን እናስብ ለኛ የሚገርመን
ü የመካከለኛው ምስራቅ ነውጥና የህዝቦች አለመረጋጋት ነወይ?
ü የግብፅ ብጥብጥና የሆስኒ ሙባረክ ከስልጣን መልቀቅ ነወይ?
ü የሊቢያ ፈተናና የሙዐመድ ጋዳፊ ጭካኔ ነወይ?
ü የሱማሊያ መበታተንና የባህር ላይ ውንብድና ነወይ?
ü የሆሳማ ቢንላደን አመፅና የመስከረሙ 1 የአሜሪካ ህንፃ መጋየት ነው ወይ?
ü ወይንስ የሶቪየት ህብረት መበታተን የዩጎዝላቪያ መለያየት የአይቮሪኮስታውያን አመጽ?
እኛ እኮ አውራቂስንም እናውቃለን፣ ኖህና የሎጥ ታሪክንም እናውቃለን፣ የእስራኤልና የፍልስጤምንም ሆነ የሮማውያንን ወረራ ከመፅሃፍ ተምረናል በምልክት የምንደነግጥና የምንቦርቅ ሳንሆን በተከፈቱ የዕምነት አይኖች የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ዳግም ምፅዐት በእምነትና በተስፋ የምንጠባበቅ ነን፡፡ ስለዚህ የጌታ ምፅዐት የሚያስደነግጠን ሳይሆን በፍቅር የምንጠብቀው ነው የሚሆነው ለዚህ ደግሞ ዝግጁ እንድንሆን መፅሃፍ እንዲህ ይለናል ፡፡
"ያን ግን እወቁ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ በነቃ ቤቱም ሊቆፈር ባልተወም ነበር፡፡ ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ የሰው ልጅ በማይታሰብበት ሰዓት ይመጣልና ፡፡" (ማቴ 24 ፡43)
ይመጣልና በእግዚአብሔር ግንዛቤና እውቀት " ይመጣል " ነው አንዳችም ክፍተት አንዳችም ጥርጣሬ አንዳችም የምናልባታዊነት ድምፀት የለውም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ የምድርን ጫፍ ከዳር እስከዳር ሊረግጥ ያለአንዳች ጥርጥር በዘመኑ ፍፃሜ ወደእኛ ያመጣዋል፡፡የምድሪቱ ፍፃሜን የሚያበስረው የደውል ድምፅ ከትላንት ይልቅ ዛሬ ከዛሬም በላቀ ሁኔታ ነገና ከነገ በስቲያ በምድራችን በጉልህ መደመጡ የማይቀር እውነት ነው፡፡እና ጥንቃቄን ለእናንተ እናስታውሳለን፡፡ ትጋትን ለናንተ " እርስ በእርስ ተመካከሩ " በተባለው መንፈስ ውስጥ ሆነን እንመክራለን፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል በጥንቃቄ በመመርመር ከቃሉ ውስጥ በሚገኝ የዘመኑን ፊት የመለየት ጥበብ ተክነን ከእግዚአብሔር ጋር ያልተቋረጠ ህብረትን እንመሰርታለን፡፡ በምድር የምንኖረው የእርሱ እውነተኛ ወኪሎች ሆነን ነውና ውክልናችንን በትክክለኛው የተልዕኮ ፈፃሚነታችን መስመር አስይዘን የምድር ጉዞአችንን ልናጠናቅቅ ተስፋ እናደርጋለን ፣ እናምናለንም ፡፡ የማንቂያው የደውል ድምፅ የሚነግረን ልዩ መልዕክት ቢኖር በትጋትና በዝግጁነት የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መመለስ እንድንጠብቅ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment