የገላትያ መልእክት ዐቢይ ዓላማ በክርስቶስ አምነው ከጸጋው ቃል ወደ ኋላ በመመለስ እውነትን ይቃወሙ ለነበሩ ምዕመናን የተጻፈ ነው፡፡ ሐዋርያው በዚህ መልእክት ላይ የተለያዩ ምሳሌዎችን በመጠቀም እንዲሁም በቀደመው ኪዳን ስለበነሩ ነገሮች በመጥቀስ የገላትያ ምዕመናን አስቀድሞ ከተሰበከላቸው የክርስቶስ ወንጌል የተለየ ወንጌልን የሚሰብክ ሰውም ይሁን መልአክ የተረገመ ይሁን!›› በማለት በሐዋርያዊ ሥልጣኑ ይገዝታል (ገላ. 1፥8)፡፡
በገበሬ እርሻ ላይ ምርጥ ዘር ከተዘራ በኋላ ዘሩ መብቀል ሲጀምር ቀድሞ ያልነበረ ነገር መታየቱ አይቀርም፡፡ ይህም የሚሆነው መልካም ነገር ሁሉ ተቃዋሚ ስላለበት ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ መልካም ነገር ኃላፊነት ነው፡፡ ጥበቃና እንክብካቤም ይፈልጋል፡፡ ያለበለዚያ ለፍሬ አይበቃም፡፡ ጌታም በእርሻው ላይ ስለተዘራው መልካም ዘር ከተናገረ በኋላ ሰዎቹ ሲተኙ ጠላት መጥቶ እንክርዳድ እንደዘራና እንደሄደ ለደቀ መዛሙርቱ ሲናገር እናያለን፡፡ (ማቴ. 13፥24-30)
በዚህ ዘመንም በእውነተኛው የወንጌል አገልግሎት ላይ እንክርዳድ ለመዝራት የተሠማሩ፣ ሕዝብ የክርስቶስን ወንጌል እንዳይሰማ በተረትና በወግ እንዲሁም የራሳቸውን የጥቅም ፍላጎት ለማሳካት በሚያመች ሁኔታ ተብትበው ሕዝብን ለባርነት የሚወልዱ ብዙ ናቸው፡፡
እነዚህ ወገኖች ቀድሞውንም የጽድቅ አገልጋዮች አይደሉም፡፡ መቼም ሰው ሁሉ ባለበት መንፈሳዊ ደረጃና ኑሮ ከታመነ፣ ይህ ሰው ለእግዚአብሔር መንግሥት ቅርብ ነው፡፡ ነገር ግን መንፈሳዊውን አገልግሎት አንድ የትርፍ መንገድ አድርጐ መያዝና ለማይኖሩበት እውነት መሟገትን የመሰለ የድፍረት ኃጢአት የለም፡፡
የክርስቶስ ወንጌልን የሚሰብኩትን ስም እየሰጡ እንዳያገለግሉ በማድረግ፣ ለክርስቶስ ክብር የሚቀርበውን የምሥጋና መሥዋዕት /ዝማሬ/ ሁሉ የሚያወግዙ፣ ይህ የእኛ አይደለም በሚል ፈሊጥ የሁሉም ነገር ጀማሪዎች እኛ እንደሆንን እንድናስብና ከእውነተኛው አምላክ እንድንለይ የሚያደርጉ፣ የክርስቶስ ስም የተጠራበት ዝማሬም ሆነ ስብከት የማይጥማቸው እነዚህ የመስቀሉ እንቅፋትና የባርነት ልጆች ናቸው፡፡
ወገኖቼ ! በወንጌል አምነናል እያልን ክርስቶስን የሚስጠላ ማንነት ካለን ስሙ ሲጠራም የምንደነግጥ ከሆንን ራሳችንን መፈተሽ ይኖርብናል፡፡ የማን ስም ይሰበክ? የማን ማዳን ይነገር? የማንስ ስም ይመስገን? በስሙ እየተጠራን እርሱን ከመቃወም ያድነን!
ሳይማሩ አውቃለሁ እንደማለት ያለ ድንቁርና የለም፡፡ የብዙዎች ችግር ይህ ነው፡፡ የሚማር መንፈስ የሌላቸውና ለመቃወም ብቻ የሚኖሩ፣ ግመል እየዋጡ ትንኝ የሚያጠሩ፣ ተረፈ ፈሪሳውያን ዛሬም ሞልተዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በገበያ ግርግር ተንጠላጥለው የቤተ-ክርስቲያንን ዓውደ ምሕረትና ልዩ ልዩ የአገልግሎት ሥፍራ የተቆጣጠሩ ሲሆን የጽዋ ማኅበራቸው አባል ያልሆነ ‹‹ኦርቶዶክሳዊ አይደለም›› በማለት ሰውን ሁሉ የአሳባቸው አገልጋይ (ባሪያ) ለማድረግ የሚተጉ ናቸው፡፡
እንደሚታወቀው የሽሽግር ወቅት /Transition Period / ተብሎ የሚጠራው ጊዜ ሲከሰት ይልቁንም የመንግሥት ለውጥ ሲደረግ የሚሞቱና ትንሣኤ የሚያገኙ ወገኖች ይኖራሉ፡፡ አንዳንዶች ወደ ድህነት ቀጠና ይወርዳሉ፡፡ ሌሎች በግርግሩ ዘርፈው ከባለጠጎች ጎራ ይቀላቀላሉ፣ አንዳንዶችም ሕይወታቸውን በማጣት ወደሞት ይሻገራሉ፡፡ በአንድም በሌላም የመጣው ለውጥ ብዙ ለውጦችን ይወልዳል፡፡
በአገራችን ታሪክም የደርግ መንግሥት ሲወድቅና አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሲተካ ይህ ሁኔታ ታይቷል፡፡ ራሱን ‹‹የቅዱሳን ማኅበር›› እያለ የሚጠራው ይህ የጽዋ ማኅበር ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ የበቃው በዚህ ግርግር ነው፡፡ እየቆየ ሲሄድ ግን ራሱን እንደ አንድ ‹‹ሲኖዶስ›› መቍጠር ጀመረ፡፡ ብዙዎችም ለባርነት ወለደ፡፡ የመጣበትን ስለረሳው የሚሄድበት ቢጠፋው አያስደንቅም፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬም በንስሓ ለመመለስ በሩ ክፍት ነው፡፡
የእግዚአብሔር ቃል፡- ‹‹በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን›› (ገላ. 5፥1) ይላል፡፡ ነጻነት ሁለንተናዊ ነው፡፡ ሰው ለተገዛለት ለዚያ ባሪያ እንደሆነም መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ሰው ነጻ ግዛት ባለመሆኑ ለአንድ ጌታ መገዛቱ የግድ ነው፡፡ በክርስቶስ ያገኘነው መዳንም ከብዙ ባርነት ነጻ የወጣንበት ሲሆን ክርስትናም ራሳችንን ለዚህ ጌታ ባሪያ አድርገን የሰጠንበት የፍቅር ግዛት ነው፡፡ ቀድሞ የማይገዛንና በእኛ ላይ ያልሠለጠነ አልነበረም፡፡ ከመዳን በፊት የነበረን መታወቂያ ሁሉ የሚያሳፍር ታሪክ መዝገብ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የጽድቅ ባሪያዎች አድርጐናል፡፡
ወገኖቼ! አገልግሎታችንን መፈተሽ ይገባል፡፡ ሆዳችን አምላካችን ሆኖ ዛሬም ጥቅም የሚገዛንና በመንፈሳዊ አገልግሎት ስም የራሳችንን ፍላጎት ለማሳካት የቆምን ከሆንን የባርነት ልጆች መገለጫ ይህ ነው፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት የጸጋና የጥሪ ጉዳይ እንጂ የትምህርት ማስረጃ (የዲፕሎምና የዲግሪ ወዘተ…) ጉዳይ አይደለም፡፡ እውቀት እንጀራ ለመብላት ይጠቅም ይሆናል፡፡ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ግን ጥሪና ጸጋ ያስፈልጋል፡፡ ሰዎችን ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት በመመልመል የቤተ-ክርስቲያን አገልጋዮች ለማድረግ ማቀድና በዚህም ቤተ ክርስቲያንን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ማሰብ፣ በገንዘብ ኃይል በመደራጀትም ተከታይ ለማብዛት ማቀድ፣ ለጊዜው አሸናፊ ሊያስመስል ይችላል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በትንሣኤው ሞትን ሳይቀር የረታ በመሆኑ የወንጌሉን የምሥራች የሚገታው የለም፡፡ የወንጌል አገልጋዮችንም በማሳደድ እውነትን ማስቀረት አይቻልም፡፡
የአብርሃም ልጆች ብዙ ቢሆኑም በዋነኛነት ግን የሚታወቁት ሁለቱ እስማኤልና ይስሐቅ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለት ልጆች የአብርሃም ልጆች ቢሆኑም የተለያየ ማንነት አላቸው፡፡ እስማኤል ከእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ውጪ የተወለደና በሥጋ ልደት የተገኘ ነው፡፡ ይስሐቅ ደግሞ አስቀድሞ የተስፋ ቃል የተነገረለትና በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል የተወለደ እውነተኛ የአብርሃም ወራሽና የተስፋው ቃል ፍጻሜ ነው፡፡
በእነዚህ ሁለት ልጆች መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፡፡ ይኸውም የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል የሚፈጸመው እንደ ቃሉ በተወለደው በኩል በመሆኑ እንደ ሥጋ ፈቃድ የተወለደው እስማኤል ይስሐቅን የሚጠላና የሚያሳድድ እንደነበር ተገልጧል፡፡ ‹‹ነገር ግን እንደ ሥጋ የተወለደው እንደ መንፈስ የተወለደውን በዚያን ጊዜ እንዳሳደደው ዛሬም እንዲሁ ነው›› (ገላ. 4፥29)፡፡
እንደ ሥጋ የተወለደ በማለት የገለጠው እስማኤልን ነው፡፡ ይኸውም እስማኤል የተወለደው አብርሃም መውለድ በሚችልበት ወቅት በአብርሃምና በሣራ ምክር ከባሪያይቱ ከአጋር ነው፡፡
በዚህ አሳብና ምክር እንዲሁም ሥራ ውስጥ እግዚአብሔር የለም፡፡ እስማኤል ቢወለድም የጠብና የሁከት ምክንያት እንጂ የቤቱ ደስታ አልሆነም፡፡ ዛሬም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ እንደ እስማኤል የተወለዱ አሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች በእግዚአብሔር ቃል የተወለዱ ሳይሆኑ በሥጋዊ እውቀትና በራስ ችሎታ እንዲሁም በሥጋ ምክር የልጅነት እውቅና የተሰጣቸው ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ ብዙዎቹ የአገልግሎት መሥፈርትን እንኳ ሳያሟሉ የአገልግሎት ሥፍራዎችን የተቆጣጠሩ ጨዋዎች ናቸው፡፡ (ጨዋ የሚለው ቃል በቤተ ክርስቲያን ቋንቋ ያልተማረ ማለት ነው)፡፡
እንደ እነዚህ ያሉ በመወለዳቸው ዛሬ ቤተ-ክርስቲያን ትታመሳለች፡፡ ሌላው ቀርቶ ገደባቸውን እንኳ ባለማወቃቸው ‹‹ቅዱስ ሲኖዶስ›› እያለ ተክተው ለመሥራት የሚያስቡና የሚያወግዙ እንዲሁም የራሳቸውን አሳብ ለማስፈጸም የሚሯሯጡ ናቸው፡፡ እስማኤል ይስሐቅን እንደ ጠላው፣ አጋርም ሣራን እንደናቀች እነዚህም ወገኖች ከእነርሱ ውጪ ያለውን እንዲሁ የሚመለከቱ ናቸው፡፡ እንደ መንፈስ ፈቃድ የተወለደው ይስሐቅ ነው፡፡ ይስሐቅ የተወለደው በእግዚአብሔር ፈቃድና ችሎታ ነው፡፡ አብርሃምም ሣራም ምንም ማድረግ በማይችሉበት ወራት የተወለደ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ለመጠራት የሚያበቃን ከእርሱ የሆነልን ነገር ብቻ መሆኑን ይገልጣል፡፡ ክርስትና የዘር ውርስ አይደለም፡፡ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር በመስማማት የተሰጠን የመዳን ጸጋ ነው፡፡ ቃሉም እንዲህ ይላል ‹‹ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም›› (ኤፌ. 2፥8)፡፡ እንግዲህ በልጅነት ለመጠራት፣ ለማገልገልና ለመውረስ የእግዚአብሔር ጸጋ ያስፈልጋል፡፡ ቃሉም ‹‹የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም›› ይላልና፡፡
ሐዋርያው እነዚህን ሁለት ልጆች በምሳሌነት ያነሣው ‹‹ዛሬም እንዲሁ ነው›› የሚለውን ለመግለጥ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንም ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ዛሬም እስማኤላውያን እንደ ተስፋ ቃሉ የተወለዱትን ሲቃወሙና ሲያሳድዱ እናያለን፡፡ ከየዓውደ ምሕረቱ፣ ከየአድባራቱ፣ ከየገዳማቱ ወዘተ፡፡ በእርግጥም እውነተኛ ኦርቶዶክሳውያን የቤተ-ክርስቲያን ልጆች ዛሬም እንደሚሰደዱ ቃሉ ያረጋግጣል፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ተስፋ ቃሉ ወራሾች እነርሱ ናቸው፡፡ ቃሉም እንዲህ ይላል፡- ‹‹የባሪያይቱ ልጅ ከጨዋይቱ ልጅ ጋር አይወርስም ባሪያይቱን ከልጅዋ ጋር አውጣት፤ ስለዚህ ወንድሞች ሆይ የጨዋይቱ ልጆች ነን እንጂ የባሪያይቱ አይደለንም›› (ገላ. 4፥30-31)፡፡
ከላይ እንደተገለጠውና ‹‹ባሪያይቱን ከልጅዋ ጋር አውጣት›› እንደተባለ ዛሬም የእግዚአብሔር ፍርድ ሲገለጥ አሳዳጆች ይወጣሉ፡፡ ልጆች ይወርሳሉ፡፡ ለውርስ የሚያበቃው ከጨዋይቱ መወለድ ነው፡፡ የሚሰደዱ እንጂ የሚያሳድዱ የክርስቶስ አይደሉም፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር !
No comments:
Post a Comment