የተቀያሚ ሰዎች ባሕርይ
1. የደረሰባቸውን በደል ድንገተኛ መሆኑን ከመቀበል በፍቅራቸው ወራትም ሲዘጋጅ እንደነበረው ያስባሉ። ነገር ግን ፍቅርና ጠብ ለየብቻ እንደሚኖሩ ሊያስቡ ይገባል። ብርሃንና ጨለማ በአንድ ጊዜ አይወጡምና።
2. የራሳቸውን ቅንነት ያስባሉ እንጂ ያን ሰው ሳያውቁ ሊበድሉት እንደሚችሉ ስለሚረሱ ጥፋቴ ምንድነው? አይሉም። የሚያስደንቀው ብበድለውስ እንዴት ይርቀኛል? ሲሉ ይቅርታ ለማድረግ ግን ፈቃደኛ አይደሉም።
3. ሰዎችን ለመቀየም ምክንያት ይፈልጋል። ከሰው ጋር ስንኖር አነዱ ዓይን ስህተትን ሲያይ አንዱ እየሸፈነ መሆን አለበት።
4. አንዴ ከተቀያየሙ በኋላ ዋጋ እንደሌለው ያምናሉ። በዓለም ላይ ግን ከተሰበረ የማይጠገን ሞት ብቻ ነው። ደግሞም እኛ የእግዚአብሔርን ይቅርታ የፈለግነው ለአንድ ጊዜ ብቻ አይደለም።
5. ነገሮችን በትክክለኛ መጠናቸው ሳይሆን አጋነው ይመለከታሉ። ስድብን አቅም ቢኖው ገድሎኛል በማለት ይለጥጡታል። የትክክለኛ ሰው ባሕርይ በደልን ሳይሆን ፍቅርን አብልጦ የሚያይ ነው።
6. ቂምን መርሳት ለወደፊቱ አለመጠንቀቅ ይመስላቸዋል። ሰውን ግን ከጥርጣሬው ይልቅ ቅንነቱ ይጠብቀዋል። ተጠራጣሪዎች እራሳቸውን ቢጠብቁም የሚፈሩት አይቀርም። እግዚአብሔር ግን ቅኖችን ይጠብቃል።
7. ይቅር ማለትን እንደመሸነፍ ይቆጥሩታል። የምንኖረው ግን ክፉውን ለማሸነፍ ለመልካም ነገር በመሸነፍ ነው። ልይቅርታ መሸነፍ ለእግዚአብሔር መሸነፍ ነው።
8. የእግዚአብሔር ምስጋና ይረሳሉ። መትረፋቸው ለምስጋና አያበቃቸውም መሞከሩ ግን ይቆጫቸዋል። እግዚአብሔር ካልጣለን በሰው መቀየም ከንቱ ነው።
9. ከተደረገላቸው በጎ ነገር ይልቅ የተደረገባቸውን ክፉ ነገር አትኩረው ያየሉ። ከ90% መልካም ነገር ለ10% ስህተት ዋጋ ይሰጣሉ። ክፋትን የሚጠብቁ ሰዎች መልካም ነገር ቢበዛም ደስታቸው በደልን በመመዝገብ ነው። ይህ ደሞ ስይጣንነት ነው።
10. ጥንካሬ የሌለው ሞራል ስላላቸው በትንሽ ነገር ይቀየማሉ። እኛ ሰው ነን እንጂ እንደ ውሻ ፊት እያየን የምንኖር አይደለንም።
11. ማንም ሰው ድካም ስላለበት የሚሸከመውን ምሥጢሩን የሚጠብቅለት ይፈልጋል። ቂመኞች ግን ሰው ስለሚርቃቸው ብቸኛ ይሆናሉ።
እንግዲህ የምንኖረው ከሰው ጋር እንጂ ከመላእክት ጋር አይደለምና የይቅርታ ሰው ልንሆን ይገባል። ስንቱን ተቀይመን እንዘልቀዋለን? ሁሉም ደከማ ነውና።
የይቅርታ ሰው ለመሆን
1. ከእግዚአብሔር በየዕለቱ ይቅርታ ፈላጊዎች መሆናቸውን ማሰብ፡
2. እልከኝነት ልባችንን በቃሉ መገሰጽ
3. እግዚአብሔር ካሳየን ምህረት እንጻር የወገኖቻችን በደል ምንም መሆኑን ማሰብ።
4. እነርሱ ልንበድላቸው የምንችለውን እኛን በደሉ እኛ ግን መልካሙን እግዚአብሔርን የበደለን መሆናችንን ማሰብ፡
5. ጠቡ የመጣው ከፍቅር በኋላ ነው፡ ስለዚህ መነሻ ዓላማችን ፍቅር እንጂ ጠብ እንዳልነበር ማሰብ።
6. ከሁሉም በላይ ለተቀየምናቸው ሰዎች መጸለይ ጥላቻን ይቀንሳል። ጸሎትም የክርስቶስን ፍቅር በልባችን ያፈሳል። ለሰይጣን እንኳን ቂም በቀል የለንም አግንቼ እንዲህ ባረግኹት አንልም አልገዛልህም የሚል እሚቢታ እንጂ። ለገዛ ወንድማችን ግን ቂም በቀል ያለን በመሆናችን ራሳችንን ልንታዘብ ይገባል።
ይቆየን(ዲ.አሸናፊ)