ገለባ ውስጥ የተደበቁትን ሁሉ ትንሽ እሳት ያስፈራቸዋል
ከፍርሐት፣ ከሥጋትና ከጭንቀት ነጻ ሆነው የሰላም እንቅልፍ ተኝተው ማደር የሚችሉት እውነትን የያዙና የሰው ደም የሌለባቸው ንጹሐን ብቻ ናቸው። ቃኤል ወንድሙን አቤልን ያለምንም ምክንያት ከገደለ ጀምሮ ፈሪና ተቅበዝባዥ ሆኖ ትንሽ ኮሽታ ሲያስደነግጠው የኖረ ሰው ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት የአቤል ደም ወደ እግዚአብሔር በመጮኹ ነበር። ዘፍ 3፡10። የጻድቅ ደም እንቅልፍ አያስተኛም።
ዳንኤልን ያለምንም በደል በተራቡ የአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ያስጣለው የጥንቷ የባቢሎን የዛሬዋ ኢራቅ ገዢ የነበረው ሜዶናዊው ዳርዮስ እንቅልፍ አጥቶ ምግብም አልበላ ብሎት ሰላሙን አጥቶ አልጋው አልመቸው ብሎ ሲሰቃይ እንዳደረ ት/ዳን 6 ቁ 18 ላይ ይናገራል። ነቢዩ ኢሳይያስ “ለክፉዎች ሰላም የላቸውም” ይላል ኢሳ 57 ቁ 21። የሰው ደም እንደ ውሃ ሲያፈሱ፣ ጻድቁን ሲኮንኑ፣ ኃጥኡን ሲያጸድቁ በፕሮፓጋንዳቸው ተሰውረው ትንሽ እድሜ ያገኙ ሁሉ ሰላም የላቸውም።
በአሁኑ ሰዓት ይህን መጻፍ የፈለግሁት አንዳድ ቡድኖች በተለኮሰባቸው የነጻነት እሳት የሚይዝቱን እና የሚጨብጡትን አጥተው እየተወራጩ ስለሆነ ወገኖቼ የፕሮፓጋንዳቸው ሰለባ እንዳይሆኑ ለመከላከል ነው። እነዚህን ገለባ ውስጥ የተደበቁትን የደም ሰዎች እንደሚከተለው አቅርቢያቸዋለሁ።
1ኛ ኢሕአዴግ
ይህ ፓርቲ ከተመሠረተ ጀምሮ ያፈሰሰው ደም ወደ ላይ እየፈሰሰ አንገቱ ደርሶ እያነቀው በሞት ፍርሐት ውስጥ የሚኖር ተስፋ የሌለው ፓርቲ ነው። ነገር ግን ጽዋው ገና ስላልሞላ በሕይወት ያለ ግዙፍ ፓርቲ ይመስላል። ኢሐዴግ የሕጻናት፣ የወጣቶች፣ የሽማግሌዎች፣ የምሑራን፣ የመሐይምናን፣ የባልቴቶች፣ የወታደሮች ወዘተ ደም ወደ እግዚብሔር እየጮኸበት እንቅልፍ ያጣ ድርጅት ነው። እውነተኛ ሰዎች ያስደነግጡታል በራሱ አይተማመንም፣ የቃየልን መንፈስ ተዋርሶ ስለሚጠንቁል ያገኘኝ ሁሉ የሚገለኝ ይመስለዋል።
ቃኤል አቤልን ከገደለ በኋላ ለእግዚአብሔር እንዲህ ሲል አመለከተ “በምድር ኮብላይ እና ተቅበዝባዥ እሆናለሁ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል” አለው እግዚአብሔር ግን ይህ ፍርሐቱ የፈራውን ሁሉ ሰው በተደጋጋሚ እንዲገል ስለሚያደርገው “ቃየልን ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው ምልክት አደረገለት ይላል” ዘፍ 3 ቁ 14-15። እግዚአብሔር ቃየልን ማንም እንዳይገድለው የሚጠብቀው ምልክት ባያደርግለትና ትንሽ እረፍት ባይሰጠው ኖሮ ቃየል የፈራውን ሁሉ በመግደል ሰዎችን በጨረሰ ነበር።
ኢሕዴግን ከአራት ኪሎ እንዳይወጣ በሩን ዘግቶ ባለፈ ባገደመው ላይ እየተኮሰ እንዲቆይ ያደረገው ያፈሰሰው የደም ብዛት ስለሚጮኽበትና “ያገኘኝ ሁሉ ይገለኛል” ከሚለው ፍርሐቱ የተነሣ ነው። ይህ የቃየል መንፈስ እንዴት ይወገድለታል?
ኢሕአዴግ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ነኝ እያለ ቢያወራም አስተማማኝ የሆነ መኖሪያ ቤት የሌለው ገለባ ውስጥ የሚኖር መሆኑን እራሱ ያውቀዋል። ስለዚህ ትንሽ እሳት እጅግ ያስፈራዋል። ለምሳሌ አረና የተባለውን የትግራይ ፓርቲ እጅግ ስለሚያስፈራው ፎርጅድ አረና ሰርቶ ዋናውን እውነተኛ ፓርቲ ለማፍረስ እየሠራ ነው። አረናን ለምን ፈራው? ሕውሐት በትግራይ ሕዝብ ስም ዘግናኝ በደሎችን የፈጸመ ኢትዮጵያን ወደብ አልባ ያደረገ፣ ባድሜን ፈርሞ የሰጠ፣ የትግራይን ምርጥ ልጆች [እነሐየሎምን]ያለምንም ምክንያት የገደለ፣ የትግራይን ሕዝብ ከጎረቤቶቹ ከኤርትራ፣ ከወገኖቹ ከአማራ፣ ከኦረሞ፣ ከሱማሌ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ብሔረሰቦች ጋር ያጋጨ ጠላት የፈጠረ ግፈኛ በመሆኑ ትግራይን ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር ሊያስታርቅና በጋራ በኩልነት በነጻነት እንድትኖር ሊያደርግ የሚችል ፓርቲ የወያኔን ግፍ ሊያጋልጥ የሚችል በመሆኑ ይፈራዋል። አረና ከኢትዮጵያውያን ጋር እንዴት መኖር እንደሚገባ የተረዳ ቀና ፓርቲ፣ ብሐራዊ እርቅን የሚደግፍ፣ አብሮ መኖር የሚፈልግ ይመስለኛል።
ወያኔ ግን በጠባዩ ነፍሰ ገዳይ ነው። እንደ አቤል ያለ ቀና ፓርቲን ስለሚመቀኝ መግደል አለብኝ ብሎ ያስባል። ኢሕአዴግ ማንም እንደማይገድለው እንደ ቃኤል ምልክት ካልተደረገለት ገና ብዙ ይገላል ባይ ነኝ። እናም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕውሃትን ፍርሃት ሊያስወግድ የሚችል ፖለቲካዊ መተማመኛ እንዲሰጡት ስል እማጸናለሁ። አጥፍቶን ከመጥፋቱ በፊት ያገኘው ሁሉ እንደማይገድለው ማረጋገጫ ያስፈልገዋል። በዚህ ወቅት ግብጽ ላይ የተለኮሰው እሳት ገለባ ቤት ውስጥ የሚኖሩትን የአፍሪካ አምባገነኖች እያስደነገጠ ነው። የኛው ሕዋሐትም ኑሮው በታላቅ ፍርሐትና በጭንቀት ነው። ከዚህ ሁሉ ለምን ከገለባ ቤት ወጥቶ እሳት ወደማያስፈራው ዲሞክራሲያዊ ጽኑ ቤት ሽግግር አያደርግም? እሳት በተነሳ ቁጥር ያዙኝ ልቀቁኝ እያለ ለምን ግራ ያጋባናል? ነፋሱ ወደ ኢትዮጵያ ከነፈሰ እሳቱ ፊቱን ማዞሩና ገለባውም መበላቱ የማይቀር ነው። ስለዚህ ገላባው ውስጥ ያላችሁ ሁሉ ከገለባው ውጡ።
2ኛ የሃይማኖት መሪዎች
የሃይማኖት መሪዎች የእግዚብሔርን ድምጽ ለሕዝብ ለማሰማት በእግዚአብሔር ወንበር ላይ የተቀመጡ የከበሩ ሰዎች ናቸው። ነገር ግን አቀማመጣቸው ለአደጋ አጋልጧቸዋል። መንግሥት መገሠጽ እግዚአብሔር ልብ ለሰጣቸው መሆኑን አውቃለሁ ስለዚህ ለምን አይገሥጹትም የሚል ፍርድ ለመናገር አልደፍርም። እኔም ከዚያ ቦታ ላይ ብቀመጥ ምን ላደርግ እንደምችል አላውቅምና በሰው ግፊት ሰማትነት እንዲቀበሉ አልመክርም። ነገር ግን መገጸሥ ባይችሉም ከኢሐዴግ ጋር መተባበራቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም። በልማት በመልካም አስተዳደር ቢተባበሩ ተገቢ ነው። እንደ ኢሕአዴግ ሆነው የኢሐዴግን ተቃዋሚዎች ንጹሐንን አሳልፈው መስጠታቸው ግን ከቃኤል ማህበር ውስጥ መገኘታቸውን ያመለክታል።
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በአሜሪካ የሚገኙት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ምርቆርዮስ 13 ጳጳሳትን በሾሙ ጊዜ የአዲስ አባባን አገልጋዮች በማዋከብ ሰላም ነስተዋቸው እንደነበር እናስታውሳለን። ዛሬም የዉጩ ሲኖዶስ ሲነሣ እንቅልፍ እንደማይወስዳቸው ብዙ ጊዜ ታዝበናል። ይህ ሁኔታ ቃኤል እና አቤልን እንድናስታውስ ያደርገናል ቃኤል ሰላም አልነበረውም አቤል ግን እረፍት ላይ ነበር። በውጭ ያለው ሲኖዶስ በውጩ ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያንን በማስተማር በመሰብሰብ አንድነቱን አጠናክሮ እሳት በሚተፉ ስባኪዎቹ ታጅቦ ወደ ኢትዮጵያ የመግባት ተስፋ ያለው ነው ይባላል። የአቡነ ጳውሎስ ሲኖዶስ ግን በ2009 ዓ.ም በተነሣው የውስጥ ክፍፍል ታላላቅ አባቶችን በሌሊት እንደ ወንበዴ ሲደባደብ ተስተውሏል። ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከገለባው ውስጥ ሊወጡ ይገባቸዋል። በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ታላላቅ ቦታዎች ላይ ተሹመው የሚገኙት የኢሕአዴግ አባላት የሆኑት ስለሆኑ ሕዝቡ የሐይማኖት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ እስራትም እንዲኖርበት እንዳይንቀሳቀስና ሃማኖታዊ ንቃት እንዳይኖረው እመቤቴ ታውቅላሃለች በሚል አጉል ተስፋ እንዲደነዝዝ ተደርጓል። ይህ ገለባ እሳት የበላው ቀን ወዮ!
3ኛ ማህበረ ቅዱሳን
ማህበረ ቅዱሳንን በየጽሑፋችን የምናነሳው ጥላቻ ስላለብን አይደልም። ኢትዮጵያን ወደ ኋላ እየጎተተ ያለ ለኢትዮጵያ የማይጠቅም አስተሳሰብ ይዞ ስለሚራመድ እንዲያስብብበት ለማድረግ ነው። አባላቱ ወንድሞቻችን ናቸው ነገር ግን አሳባቸው እጅግ በጣም የተባለሸ ነው። መንፈሳዊ ነገር የተማሩ ቢመስሉም ምንም የሚያውቁት አንዳች ነገር የለም። አባላቱ የማህበረ ቅዱሳን አባላት የሆኑት መንፈሳዊ ነገር ተረድተው ሳይሆን የፕሮፓጋንዳ ሰላባ በመሆናቸው ነው። የሚማሩት ሃይማኖታዊ ፖለቲካ እንጂ የእግዚአብሔርን ፈቃድ አይደለም። የሳይኮሎጂ ችግር ውስጥ ገብተዋል። ይህን ለማረጋገጥ አንድ ነገር እንድታስተውሉ ልጠቁማችሁ።
እነርሱ ባሉበት ሁሉ ሰላም የለም። ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ ለራሳቸው ማምለክ ሳይሆን የሚፈልጉት የሌሎችን አለባበስ፣ አዘማመር፣ ካህናቱ ቅዳሴ ገብተው እስኪወጡ ድረስ እንቅስቃሴያቸውን መከታተል፣ ቃጭሉ ምን ያህል ጊዜ እንደተመታ፤ መጋረጃው መቸ እንደተዘጋ እና እንዳልተዘጋ ማየት፤ የሁሉንም ምእመናን የአምልኮ ሁኔታ መቆጣጠር፤ ትክክል አይደለም ያሉትን ለማስተካከል በመከራከር የሃይማኖት ፖሊስ መሆን ይፈልጋሉ። በዚህ አሰልቺ ክርክራቸው ስንቱ ክርስቲያን እቤቱ ቀርቷል?። ሰርግ ላይ ሲገኙ ማን ምን እንደለበሰ የሚቆጣጠሩት ማህበረ ቅዱሳኖች ናቸው። በሰርጋቸው ላይ ከውሃ በቀር ሌላ እንዲጠጣ አይፈልጉም። በቬሎ የተጋቡ ሙሽሮችን አጥብቀው ያወግዟቸዋል።
በሰዎች ላይ መከፋፈልንና የሳይኮሎጂ ችግር ሊያመጣባቸው የሚችለውና ዋናው የማህበረ ቅዱሳን የፍርኃት ትምህርት “ተሃድሶዎች እትዮጵያን ሊያጠፉ የመጡ ናቸው” የሚለው ነው። ይህ ፕሮፓጋንዳ በኦርቶዶክሳውያን መካከል መተማመን እንዳይኖር ከሳሽ እና ተካሽ ሆነን እንድንከፋፈል አድርጎናል። ፍርሐትን እንጂ እምነትን አይማሩም፤ በዚህ ምክንያት በአብያተ ክርስቲያናት ሰላም ጠፍቷል እስከ አሁን ያልበረደው የአዋሳ ገብርኤል ብጥብጥ በማህበረ ቅዱሳን የሚመራ ነው። በአሜሪካ በዳላስ ሚካኤል ዱላ እስከመማዘዝ ደርሰዋል። የውጭው ሲኖዶስ ጨርሶ ስላባረራቸው በሰላም እየኖረ ነው ከዚያ በፊት ግን በነዳንኤል ክብረት አዝማችነት ከፍተኛ ሁከት ነበር።
ዛሬ በነሱ ላይ ለመጻፍ የተነሳሳሁበት ምክንያት ደጀ ሰላም በተባለው “ጸረ ሰላም” ድረ ገጻቸው ላይ “የተሃድሶ ወጥመድ” የሚል ሐሳብ ያለው ጽሑፍ ካነበብሁ በኋላ ነው። ይህ ፕሮፓጋንዳ ኦርቶዶክሳውያን እርስ በርሳቸው እንዳይተማመኑ የሚያደርግ ተንኮል ስለሆነ ወገኖቼን ተተንቀቁ ለማለት ነው።
ኢሕዴግን ዲሞክራሲ የሚያስፈራውን ያህል ማህብረ ቅዱሳንንም ወንጌል ያስፈራዋል። ኢየሱስ የሚል ስም ያስደነግጠዋል፤ ወንጌል የኃጢአትን ቆሻሻ የሚያቃጥል እሳት መሆኑ የታወቀ ነው። ማህበረ ቅዱሳን ወንጌልን የሚፈራው ገለባ ውስጥ ተደብቆ ስለሚገኝ ነው። ገድላት እና ድርሳናት በሚል ጭፍን ፕሮፓጋንዳ ይዘታቸውን የማያስተውለውን ሕዝብ በማሰለፍ የገንዘብ ምንጫቸው ስላደርጉት ወንጌል ሲሰበክ አይወዱም “ኢየሱስ ጌታ አዳኝ” የሚሉ ሰዎች ሁሉ ተሃድሶዎች ስለሆኑ አትስሟቸው ብለው አባላቱቹን አሳውረዋቸዋል።
እውነቱን የተረዱ ወጣቶች የቤተ ክርስቲያናቸውን ችግር ለይተው ያስተዋሉና ቤተ ክርስቲያናችንን አንለቅም ብለው የቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን እውነቱን አውቀው ወደ ሌላ ሃይማኖት እንዳይፈልሱ በቅንነት እየተጉ ያሉትን ወገኖች ስማቸውን በመበከል መከራ ሊያመጡባቸው ይፈልጋሉ። ከሣቴ ብርሃን የተባለውን ኮሌጅ እና ቅድስት ሥላሴን መጥፎ ጥላሸት እየቀቡ ናቸው። እነዚህ የቤተ ክርስቲያናችንን ተስፋዎች ድርሳን እና ገድል ካላነበባችሁ ተብለው እንደዚህ የሚወገዙት ለምን ይሆን? እስልምና አገር እየወረረ ባለበት በዚህ አሳዛኝ ወቅት ሰባኪዎቻችንን ተቀባይነት እንዲያጡ የሚድረገው ሥራ ሰይጣናዊ ሥራ እንጂ ሌላ ፋይዳ አይገኝበትም።
እነዚህ ወንድሞቻችን ትምህርት ቤት የገቡት ከሕዝቡ የተሻለ አስተሳሰብ እንዲያገኙና ሕዝብን ካለበት ችግር እንዲያላቅቁ ታስቦ እንጂ ባሉበት ላይ እየረገጡ ጎታች ቡድኖች እንዲሆኑ አይደለም። የመንፈሳዊ ኮሌጆቻችን ተማሪዎች መለወጥ ለቤተ ክርስቲያናችን ተስፋ ነው። ዘኬ በመብላት ጊዜያቸውን ከሚያባክኑ 500000 [አምስት መቶ ሺህ] ካህናት ውስጥ የለውጥ ሰዎች ማግኘታችን እድሎኞች ያደርገናል እንጂ የሚጎዳን አይደለም። እነርሱ ቤተ ክርስቲያን በጥራት መጓዝ እንዲኖርባት ለማስተካከል የሚታገሉ እንጂ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት እንዳልሆነ ለማንም ግልጽ ነው።
ማህበረ ቅዱሳን እውነት መስሎት ልጄ ልጄ እየተባለ ሲቆላመጥ በነበረበት ወቅት በትውልዱ ላይ ያን ሁሉ ቆሻሻ ትምህርት ዘርቶ አሁን እውነቱ እየወጣ ሲጋለጥ ስም በማጥፋት ጊዜውን ለማራዘም ይታገላል። ካፈርሁ አይመልሰኝ እንደሚባለው መረጃ አገኘሁ ሊያጠፉን ነው በማለት ይጮኻል።
በመሠረቱ ማህበረ ቅዱሳን ለተሰጡት አስተያየቶች መልስ መስጠት አለበት። በ abaselama.org ላይ የቀረቡት ትችቶች መልስ አልተሰጠባቸውም። “የዶሮ ጭንቅላት መብላት እንደ ቅባ መንግሥት ሆኖ በገድለ ተክለሃይማኖት ላይ መገለጡ ከምን የተቀዳ ልምምድ ነው?” ለሚለው ጠንካራና ግልጽ ጥያቄ መልስ መስጠት ያስፈልጋል ወይም መጽሐፉን አንቀበለውም የኛ አይደለም ማለትም አንድ መልስ ነው። ከዚህ አልፎ ግን ባዶ ፕሮፓጋንዳ መንዛት ያልበላውን ማከክ ነው። እውነቱን መደበቅ አይቻልም። ማህበረ ቅዱሳን እውነቱን በመሸሽ በፕሮፓጋንዳው እቀጥላለሁ ካለ ግን በተጨባጭ አሁን እየተደረጉ ያሉ አስከፊ የሚባሉ ሃይማኖታዊ ሽፋን ተሰጥቷቸው የሚፈጸሙትን ምሥጢራዊ ወንጀሎችን ወደ አደባባይ እንዲወጡ ያደርጋቸዋል። ይልቁንስ ተሃድሶ እያለ ከሚከሳቸው ወንድሞቹ ጋር በመወያየት ክርስትናው በኢትዮጵያ የሚስፋፋበትን መንገድ በጋራ መፈለግ፣ መታረም ያለባቸው እንዲታረሙ መርዳት፣ አጉል ኩራት አይሆንም እራት እንደተባለው የሁለት ሺህ ዓመት ታሪክ አለኝ የሚለውን ትምክህት ትቶ ዛሬ የጌታን ፈቃድ ቢፈጽም ይሻለዋል።
አንዳድ አስተያየት ሰጭዎች ተሃድሶዎች ኦርቶዶክስን ትተው ፕሮቴስታንቱን ለምን አያድሱም ይላሉ። እነርሱ ስለቤታቸው እንጂ ስለጎረቤታቸው የሚያገባቸው ነገር የለም። የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች እንደተባለው መሆን አይፈልጉም።
ማህበረ ቅዱሳን እንደሚያወራው ተሃድሶዎች ቤተ ከርስቲያኒቱን ለማፈረስ ሳይሆን ከወደቀችበት ለማንሳት ትልቅ ሸክም ያለባቸውና ወደ ጥንታዊ ማንነቷ እንድትመለስ የሚደክሙ ናቸው።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!
በተስፋ አዲስ
No comments:
Post a Comment