Tuesday, February 15, 2011

ባሪያዎች ሊያረጉን (የገላትያ መልእክት ም 2፡6-14) ክ.3 ዲ. ተከስተ ጫኔ

የገላትያ መልእክት ም 2፡6-14

አለቆች የመሰሉት ግን በፊት ማን እንደነበሩ አይገደኝም እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ
አያዳላም አለቆች የመሰሉት አንዳች እንኳ አልጨመሩልኝምና (ቁ. 6)
በዚህ እርስ ውስጥ የጳውሎስን እና የዋና [የመጀመሪያዎችን] ሐዋርያት ስምምነት እና አንድነት
እንማራለን። ሙሉውን ቃል እንደሚከተለው ያንቡ፥
አለቆች የመሰሉት ግን፥ በፊት ማን እንደ ነበሩ አይገደኝም፤ እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ
አያደላም፤ አለቆች የመሰሉት አንዳች እንኳ አልጨመሩልኝምና፥ ተመልሰው ግን ጴጥሮስ ለተገረዙት
የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠው እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠኝ
አዩ፤ ለተገረዙት ሐዋርያ እንዲሆን ለጴጥሮስ የሠራለት፥ ለእኔ ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ እንድሆን
ሠርቶአልና። ደግሞ የተሰጠኝን ጸጋ አውቀው፥ አዕማድ መስለው የሚታዩ ያዕቆብና ኬፋ ዮሐንስም እኛ
ወደ አሕዛብ እነርሱም ወደ ተገረዙት ይሄዱ ዘንድ ለእኔና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤ ድሆችን
እናስብ ዘንድ ብቻ ለመኑን፥ ይህንም ደግሞ ላደርግ ተጋሁ። ነገር ግን ኬፋ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ ፊት
ለፊት ተቃወምሁት፥ ይፈረድበት ዘንድ ይገባ ነበርና። አንዳንድ ከያዕቆብ ዘንድ ሳይመጡ ከአሕዛብ ጋር
አብሮ ይበላ ነበርና፤ በመጡ ጊዜ ግን ከተገረዙት ወገን ያሉትን ፈርቶ ያፈገፍግ ነበርና ከእነርሱ ተለየ።
የቀሩትም አይሁድ ደግሞ፥ በርናባስ ስንኳ በግብዝነታቸው እስከ ተሳበ ድረስ፥ ከእርሱ ጋር አብረው
ግብዞች ሆኑ። ነገር ግን እንደ ወንጌል እውነት በቅንነት እንዳልሄዱ ባየሁ ጊዜ በሁሉ ፊት ኬፋን። አንተ
አይሁዳዊ ሳለህ በአይሁድ ኑሮ ያይደለ በአሕዛብ ኑሮ ብትኖር፥ አሕዛብ በአይሁድ ኑሮ ሊኖሩ እንዴት
ግድ አልሃቸው? አልሁት። (ገላ ፪፥ ፮ - ፲፬)
በዚህ ንባብ ውስጥ እውነት አለቅነትን እንኳ ያላግባብ ከሆነ የማታከብር መሆኗን እንረዳለን። አለቅነት
ከወንጌል እውነት ጋር ሲሆን ማዕረግ ነው። ከወንጌል እውነት ውጭ የሆነ አለቅነት ግን ሙስና ነው።
ሐዋርያው ጳውሎስ ዋነኞቹ ሐዋርያት ከጌታ ጋር በነበሩበት ዘመን አብሮ ባይኖርም አለቅነታቸውን
አልካደም ይህም በወንጌል እውነት ጸንተው በመገኘታቸው እንጂ ዝም ብለው አለቃ ስለሆኑ አይደለም።
የወንጌልን እውነት ባይዙ ኖሮ የነርሱ አለቅነት ለጳውሎስ ጉዳዩ አልነበረም። አለቆች በፊት ማን እንደነበሩ
አይገደኝም እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ አያዳላምና ይላል። ደግነቱ ግን ጳውሎስ ወደ ዋነኞቹ
ሐዋርያት ገብቶ የሚሰብከውን ወንጌል ባሳወቃቸው ጊዜ ምንም ስሕተት እንደሌለበት ማረጋገጣቸው
ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ፤ ሐዋርያው ዮሐንስ፤ ሐዋርያው ያዕቆብ አዕማድ መሆናቸውን ጳውሎስ
ተናግሯል። አዕማድ ማለት ምሰሶዎች ማለት ሲሆን በዚህ ክፍል ውስጥ ዋነኛ አለቆች ለማለት ነው።
ጌታ ወደ ቅዱሱ ተራራ ይዞ ወጥቶ በርሃነ መለኮቱን ያሳያቸው ሐዋርያት እኒህ ሦስቱ ናቸው። (ማቴ 17፡
1) የሙክራቡ አለቃ ሴት ልጅ በሞተች ጊዜ ሊያስነሳት ወደ ቤት ሲገባ እነዚህን ሦስት ሐዋርያት አስከትሎ
ነበር የገባው። በጌቴ ሴማኒ የአትክልት ቦታ በሚጸልይ ጊዜ እኒህን ሦስት ሐዋርያት ነበር ይዞ
የሄደው።(ሉቃ 26፡37)። እነዝህ ሦስት ሐዋርያት ከዘጠኙ የበለጠ ምሥጢር የሚያዩ ነበሩ። አዕማድ
የሆኑት በዚህ ምክንያት ነው። ሆኖም ግን እግዚአብሔር በሐዋርያቱ መካከል አድልዎ አያድርግም
ሥራዓትን መሥራቱ ነበር እንጂ። ሐዋርያው ጳውሎስ በደማስቆ መንገድ ላይ ለሐዋርያነት ሲሾም እነዚህ
ሦስት ሐዋርያት አያውቁም ነበር ነገር ግን በአሕዛብ መካከል ይሰብክ የነበረውን ወንጌል ይሰሙ ነበር።
አንድ ቀን ግን በበርናባስ አስተዋዋቂነት በኢየሩሳሌም ተገናኝተው ስለ ወንጌል እውነት ተወያዩ። በዚህ
ጊዜ ለጳውሎስ የተሰጠውን ጸጋ አስተዋሉ እግዚአብሔር ለአሕዛብ የሾመው ሐዋርያ እንደሆነ ተገነዘቡ።
ጳውሎስ የሮሜ ዜግነት ስለነበረው የአሕዛብን ልማድ ጠንቅቆ ያውቃል። ስለዚህ የአሕዛብ ሐዋርያ ሆኖ
ተሾመ ይህ ማለት ግን የአሕዛብ ሐዋርያ ብቻ ማለት ሳይሆን አብዛኛውን የአገልግሎቱን መሥመር በዚያ
አደረገለት ማለት ነው።ጴጥሮስ ደግሞ የአይሁድን ልማድ ስለሚያውቅ አይሁድን እንዲያገለግል
አብዛኛውን አገልግሎት ለአይሁድ እንዲያደርገው መሥመሩን በዚያ ሠራለት።
ጳውሎስ ለአይሁድ የሆነው ወንጌል፤ ለአሕዛብ የሆነው ወንጌል ሲል አቀራረቡ እንደልማዳቸው የሆነ
ጳውሎስ ለአይሁድ የሆነው ወንጌል፤ ለአሕዛብ የሆነው ወንጌል ሲል አቀራረቡ እንደልማዳቸው የሆነ
ለማለት እንጂ የተለያየ መልእክት ያለው ወንጌል ተቀበልን ለማለት አይደለም። ወንጌል ሰማያዊ የሆነ
አንድ መልእክት አለው መልእክቱም በክርስቶስ የሆነ የዘለዓለም ሕይወት ነው። መጥፎውን፤ ባዕድ
አምልኮ ያለበትን ልማድ እና ባሕል እንጂ ጥሩውን ፤ በጎ የሆነውን እና ጉዳት የሌለውን ልማድ
አያፈርስም። በተለይም በአሕዛብ እና በአይሁድ መካከል የነበረው ልዩነት የመብል ጉዳይ ስለነበር
እግዚብሔር የመብል ልማዳቸውን መሠረት አድርጎ ሳይሆን ፍቅሩን ብቻ መሠረት አድርጎ በጸጋው
ሁለቱንም ተቀብሏቸዋል (ሮሜ 14፡1-5) ስለዚህ አይሁድ የማይበሉትን እንዲበሉ አይገደዱም አሕዛብም
የሚበሉትን እንዲተው አይገደዱም ይህ የባህል እንጂ የወንጌል ጉዳይ አይደለም።
እግዚአብሔር አድራሻችንን ሁኔታችንን ባህላችንን ያውቃል በዚህ እንዳለን ግን አንዱን የወንጌል እውነት
በአድራሻችን ባለንበት ባህል እና ሐገር ልኮልናል። ለአይሁድ ጴጥሮስን ለአሕዛብ ደግሞ ጳውሎስን
ልኮአል። ለእኛም ለኢትዮጵያውያን ባለንበት ሥፍራ ባለንበት ባህል ወንጌልን ልኮልናል። ታዲያ በወንጌል
እውነት የሕይወጥ ለውጥ እንዲመጣ መስበካችንን ትተን የባህል ለውጥን የምንሰብክ ከሆነ ብጥብጥን
እንጂ ሰላምን አናመጣም። አንዳዶች የባህል ለውጥን ለማምጣት ሲታገሉ የወንጌልን እውነት የረሱት
ይመስለኛል ለዚህ ነው የባህል ለውጥ እንጂ የሕይወት ለውጥ ማየት ያልቻልነው። እግዚአብሔር
አይሁድን በአይሁድነታቸው አሕዛብን በአሕዛብነታቸው በክርስቶስ በኩል ከተቀበለ። እኛን
ኢትዮጵያውያንንስ በኢትዮጵያዊነታችን በክርስቶስ በኩል እንዴት እንዲያው አይቀበለን? ታዲያ ከባህል
ለውጥ ጋር ግብ ግብ ከመግጠም ከሌላው የጥላቻ እና የክፋት ኃይል ጋር መዋጋት አይሻልምን? አዕማድ
ሐዋርያት የእግዚአብሔርን አሠራር ተረድተዋል እነርሱ ወደ ተገረዙት ጳውሎስ እና በርናባስ ደግሞ ወደ
አሕዛብ እንዲሄዱ ቀኝ እጃቸውን ሰጡአቸው (ቁ. 9)። ቀኝ እጅን መስጠት ስምምነትን ያመለክታል ቀኝ
እጅ ለወዳጅ እንጂ ለጠላት አይሰጥምና ። የወንጌል እውነት ያስማማል የወንጌል እውነት ከሌለን ግን
የቱንም ያህል ብንቀራረብ አንድ ልብ ሊኖረን አይችልም።
ዛሬ በዚህ ዘመን ያለን ክርስቲያኖችም ሌላውን የርስ በርስ ጦርነት እንተወውና በወንጌል እውነት ላይ
እንስማማ የወንጌልን እውነት ለዓለም እንንገር ያልተላክንበትን ስናወራ የተላክንበትን መርሳት የለብንም።
ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ ተብለናል። ጴጥሮስ እና ጳውሎስ በአንድ ወቅት በወንጌል እውነት
ምክንያት ተጋጭተው ነበር። ጴጥሮስ አይሁድ በማይኖሩበት ጊዜ ከአሕዛብ ጋር አብሮ ይበላል አይሁድ
በሚመጡበት ጊዜ ደግሞ በነገሩ እንዳላመነበት ለማስመሰል ከአሕዛብ ይለያል። በብሉይ ኪዳን ዘመን
አይሁድ ከአሕዛብ ጋር አይተባበሩም ነበር። አሁን ግን ያ የጥል ግድግዳ በክርስቶስ ደም መፍረሱን እና
ሁለቱ በክርስቶስ አንድ መሆናችውን ወንጌል ይናገራል
"ስለዚህ እናንተ አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ
የተባላችሁ፥ ይህን አስቡ፤ በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን
እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ
ነበራችሁ። አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም
ቀርባችኋል። እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ
በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ
ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል
ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው። መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው
ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፤ በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት
አለንና። እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ
እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም" (ኤፌ 2፡11-19)።
እንግዲህ ቅዱስ ጴጥሮስ ለዚህ የወንጌል እውነት ጸንቶ ሊቆም ባለመቻሉ ቅዱስ ባውሎስ ፊት ለፊት
ተቃውሞታል እንዲያውም ፍርድ ይገባው ነበር በማለት ይናገራል። ጴጥሮስ አይሁድን ሲያይ እንደ
አይሁድ አሕዛብን ሲያገኝ እንደ አሕዛብ መሆኑ ከመካከላቸው የተወገደውን የጥል ግድግዳ እና
በክርስቶስ የተመሠረተውን ሰላም የሚሸረሽር ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ ባይቃወመው ኖሮ ይህ የወንጌል
እውነት በሁለቱ ማለት በአይሁድ እና በአህዛብ ዘንድ ሥፍራውን ባጣ ነበር። በርናባስም በዚህ አይነቱ
እውነት በሁለቱ ማለት በአይሁድ እና በአህዛብ ዘንድ ሥፍራውን ባጣ ነበር። በርናባስም በዚህ አይነቱ
ግብዝነት ትስቦ ነበር። ወንጌል ግን እውነት ነውና ያሸንፋል።
“አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤
ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና። እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም
ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ” (ገላ 3፡28-29)።
የሚለው የወንጌል እውነት ነው። ይህ አንድነት የመጣው በክርስቶስ ደም ነው። ስለዚህ እንደገና የጥል
ግድግዳን መሥራት የክርስቶስን ደም ከንቱ ማድረግ ነው። እኛም በዚህ ዘመን የምንገኝ ክርስቲያኖች
በሚያምኑ እና የክርስቶስ አካል በሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች መካከል በባህላቸው እና በሥራዓታቸው
ምክንያት ጠብና ጥላቻን መገንባት የለብንም። ሁሉም ወደ እግዚአብሔር የመጣው በክርስቶስ እንጂ
በባህሉ እና በዘሩ አይደለም እንጠንቀቅ።
እኛ በፍጥረት አይሁድ ነን ኃጢአተኞችም የሆኑ አሕዛብ አይደለንም (ቁ. 15)(... ይቀጥላል)

No comments:

Post a Comment