የገላትያ መልእክት ም 2፡4-5
ነገር ግን ባሪያዎች ሊያደርጉን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለንን አርነታችንን ይሰልሉ ዘንድ
ሾልከው በስውር ስለ ገቡ ስለ ሐሰተኞች ወንድሞች ነበረ። የወንጌልም እውነት
በእናንተ ዘንድ ጸንቶ እንዲኖር ለአንድ ሰዓት እንኳ ለቅቀን አልተገዛንላቸውም። (ገላ
2፡4-5)።
ባሪያ መሆን ከባድ ነው። ባርነት በጥንት ዘመን እራስን የማጣት ያህል አስከፊ ነበር። ባሪያ
የጌታው ንብረት ነው። በቤት ውስጥ እንዳለ እንደ አንድ ጠቃሚ እቃ ወይም እንሥሣ እንጂ
እንደ ሰው ሆኖ በክብር አይታሰብም ነበር። ባሪያ ለጌታው ሥራ በሚሠራበት ጊዜ የታዘዘውን
ማድረግ ብቻ እንጂ ለምን ጉዳይ ያን እንደሚያደርግ መጠየቅ አይፈቀድለትም ነበር። “ ባሪያ
ጌታው የሚያደርገውን አያውቅም” ይላል (ዮሐ 15፡15)። ይህ ዓይነቱ ባርነት መንፈስን
የሚጎዳ ሥርዓተ ባሪያ ቢሆንም የሥጋ ባርነት ነው።
በጣም አስከፊው ባርነት ግን የመንፈስ ባርነት ነው በተለይም ሕይወትን በማይሰጥ ሃይማኖት
በሚመስል ወግ እና ልማድ መታሠር አስከፊ ባርነት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ባሪያዎች
ሊያደርጉን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለንን አርነት ሊሰልሉ” ሲል በትክክል ሰው ሊፈጽመው እና
ሊጸድቅበት በማይችለው በሙሴ ሕግ በማሠር በክርስቶስ ያገኘነውን የሕይወት ነጻነት
ሊያሳጡን ይፈልጋሉ ለማለት ነው።
ሐዋርያው ቅ/ጴጥሮስ በኢየሩሳሌሙ ሲኖዶስ ላይ ስለሙሴ ሕግ ሲናገር እንዲህ ነበር ያለው
“እኛ እና አባቶቻችን ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በደቀ መዛሙርት ጫንቃ ላይ
በመጫን እግዚብሔርን አሁን ስለምን ትፈታተናላችሁ?” (የሐዋ 15፡10)።
አይሁድ አባቶቻቸው እና እነርሱ ያልቻሉትን ቀንበር በገላትያ ክርስቲያኖች ላይ ለመጫን
ሞክረው ነበር። ቀንበር በሬ የሚጠመድበት እቃ ሲሆን በሬው ቀንበር ውስጥ ከገባ በኋላ
ምንም ነጻነት ስለሌው አንገቱ እስኪመለጥ ድረስ የማይችለውን ሁሉ ሲጎትት ይውላል።
መንፈሳዊ ነገርም ሕግ እና ግዴታ ሲበዛበት ቀንበር ሆኖ የማይቻል ነገር ይሆናል። ሰዎችም
ከዚህ ቀንበር ውስጥ ላለመግባት ሲሉ ከሃይማኖት ይሸሻሉ። የገቡትም ቀንበሩ ሲከብዳቸው
የተለያየ ምክንያት በመደርደር በኃጢአት ይወድቃሉ። ከክርስቶስም ይሸሻሉ ከዚያም
የኃጢአት ባሪያ ሆነው ይኖራሉ። በክርስቶስ ያላቸውን አርነት ያጣሉ። በፍቅር እና በደስታ
ሳይሆን በግዴታ የሚደረግ ማንኛውም ነገር ባርነት ነው።
ክርስቶስ ከምንድር ነው ነጻ ያወጣን?
* በመጀመሪያ ከኃጢአት ባርነት ነጻ አውጥቶናል “ኃጢአትን የሚያደርግ የኃጢአት ባሪያ
ነው”(ዮሐ 8፡34)። እንደተባለ ኃጢአተኛ ባሕርያችን በአዲስ ልደት፤ በአዲስ ተፈጥሮ
ስለተዋጠ የኃጢአት ባሪያ ከመሆን ነጻ ወጥተናል ይህን ያደረገውም የክርስቶስ ጸጋ ነው።
ኃጢአትን እንዳናደርግ ብናደርግም እንኳ ንስሐ እንድንገባ የሚያስችል ኃይሉን ሰጥቶናል።
ኃጢአት እረፍት አይሰጥም ሰላምም የለውም ክርስቶስ ግን ከኃጢአት ነጻ በማውጣት እረፍት
እና ሰላምን ሰጠን።
* ሁለተኛ በሕግ ምክንያት ከሚመጣ የሞት ፍርድ ነጻ አወጣን። በሮሜ 7፡10 ላይ “ለሕይወት
የተሰጠችውን ትእዛዝ [ሕግ]ለሞት ሆና አገኘኋት” እንዳለ። ሕግ ለሕይወት ቢሰጥም ሰው
ከባሕርዩ የተነሳ መፈጸም ስለተሳነው የሚጸድቅበት ሳይሆን የሚሞትበት ሆነ። ስለዚህ
ኢየሱስ ክርስቶስ የኛን ሞት በመሞት የሕግ ፍጻሜ ሆኖ ነጻ አወጣን።
“የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውንም ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ፥ ለእግዚአብሔር
ጽድቅ አልተገዙም። የሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና"
ይላል። (ሮሜ 10፡3-4)። በደብረ ሲና የተሰጠው ለሞት ሲሆን በቀራንዮ ላይ እራሱን የሰጠው
ክርስቶስ ግን ሕይወትን ሰጠን።
* ሦስተኛ ከሠይጣን ክስ እና እሥራት ነጻ አወጣን። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ብርሃን ሆኖ
ከመምጣቱ በፊት በጨለማ ውስጥ ነበርን። ሰይጣንም ጨለማውን ተገን አድርጎ የራሱን
አገዛዝ ይጭንብን ነበር ኤፌ 2፡1-3። አሁን ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንረግጠው ዘንድ
ሥልጣን አገኘን። “ያመኑትንም እንዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል በስሜ አጋንትን ያወጣሉ”
ይላል።(ማር 16፡17)። በስሙ ከሰይጣን እሥራት ነጻ ወጥተናል።
ነገር ግን ሰው ቀንበር ሲከብድበት መንፈሳዊ ኃይሉ ይደክማል ከዚያም ሊያድነው የማይችል
ሕግን ሁሉ ያወጣል በኃጢአትም ይወድቃል፤ በመጨረሻም በራሱ መንገድ እረፍት ሲያጣ
ተስፋ ይቆርጥና ከክርስቶስ ተለይቶ ይኖራል። እንዴት ያሳዝናል?
እንግዲህ ሐዋርያው “ባሪያዎች ሊያደርጉን በክርስቶስ ያለንን አርነት ሊሰልሉ” ሲል
አይሁድ በኢየሩሳሌሙ ጉባኤ ላይ በሐዋርያት ከተረቱ በኋላ በሥውር ሾልከው ወደ ገላትያ
እና ወደ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት በመግባት የሙሴን ሕግ ያስተምሩ ነበር። ይህንም
የሚያደርጉት ክርስቲያኖችን ለእግዚአብሔር ባሪያ ከመሆን አስወጥተው የራሳቸው ባሪያ
ሊያደርጓቸው ስለሚፈልጉ ነው። ጳውሎስ እንዲህ ዓይነቱን ውድቀት ለመከላከል እና
በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት በማጠንከር የእግዚአብሔር ባሪያዎች እንዲሆኑ ለማደረግ
ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጓል።“የውንጌልም እውነት በእናንተ ጸንቶ እንዲኖር ለአንድ ሰዓት
እንኳ ለቀን አልተገዛንላቸውም” ይላል (ገላ 2፡5)። እኛም አርነታችንን አሳልፈን ላለምሰጠት
መጠንቀቅ አለብን። በክርስቶስ ያለንን አርነት ካጣን የኃጢአት ባሪያዎች ልንሆን ስለምንችል
የወንጌልን እውነት ጠንቅቀን ማወቅ አለብን።
የወንጌል እውነት ምንድን ነው? (... ይቀጥላል)
No comments:
Post a Comment