Tuesday, February 15, 2011

ባሪያዎች ሊያረጉን (የገላትያ መልእክት ም 2፡4-5 (ክፍል ፪) ዲ. ተከስተ ጫኔ

ባሪያዎች ሊያረጉን (የገላትያ መልእክት ም 2፡4-5 (ክፍል ፪)

የወንጌል እውነት ምንድን ነው?
“የወንጌልም እውነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶ እንዲኖር አንድ ሰዓት እንኳ ለቀን አልተገዛንላቸውም” (ገላ 2፡5)።
ጳውሎስን በጽናት ሊያቆመው የቻለው የወንጌል እውነት ነው። ሰው እውነትን አረጋግጦ ካልያዘ በትንሽ ነገር
ሊወድቅ ይችላል። እውነትን የያዘ ሰው የምሥክርነት አቋም ብቻ ሳይሆን በያዘው እውነት ላይ የመኖር ችሎታ
አለው። ለምሳሌ እምነቱ በሚሰጠው ትርጉም መሠረት ቅድስና ጽድቅ ፍቅር እና ሰላም ዋና ሕይወቱ ናቸው።
ጳውሎስም ከአይሁድ ጋር ስለአለው የሁለቱ ኪዳናት ክርክር ብቻ ሳይሆን በጽድቅ እና በቅድስናም ጸንቶ የኖረ
ሰው ነው። የወንጌል እውነት በሚመሰክርላቸው ሰዎች ጸንቶ የሚኖረው ስለ ወንጌል ባለው እውቀት መታገሉ
ብቻ ሳይሆን ሙሉውን የወንጌል እውነት በሕይወቱ ሲገልጠው ጭምር ነው።
እኛም ዛሬ በዚህ ዘመን የምንገኝ ክርስቲያኖች የወንጌልን እውነት በትክክል መረዳት እና በጽናት መቆም
አለብን። ይህን የወንጌል እውነት እንደሚከተለው ለመግለጥ እሞክራለሁ።
የወንጌል እውነት “ክርስቶስ ኢየሱስ ኃጢአተኞችን ሊያድን ወደ ዓለም መጣ” የሚለው ቃል ነው (1ጢሞ 1፡
15)። በዚህ ቃል ውስጥ ትኩረት ሰጥተን የምንመለከታቸው:
* “ወደ ዓለም መጣ”
* “ኃጢአተኞችን ሊያድን”
የሚሉትን ቃላት ነው።
ወደ ዓለም መጣ: ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን የፈጠረ፤ በሰማይ እና በምድር ያሉትን ሁሉ ያዘጋጀ ፈጣሪ ነው
(ዮሐ 1፡1-3, ቈላ 1፡15-18)። በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል የአብ ልጅ ነው። ወደ ዓለም በሥጋ ከመምጣቱ
በፊት በዓለም የነበረ ነው። ይህ የወንጌል እውነት ነው።
“ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር፤ በዓለም ነበረ፤ ዓለሙም በእርሱ ሆነ
ዓለሙም አላወቀውም” ይላል (ዮሐ 1፡9-10)።
ወደ ዓለም መጣ ማለት በሥጋ ፍጹም ሰው ሆኖ ተገለጠ ማለት ነው ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው
ፍጹም አምላክ ነው። ይህ የወንጌል እውነት ነው። ይህን የወንጌል እውነት የማያምን ሰው ክርስቲያን ነኝ
ማለት አይችልም ይህን የማያስተምርም ከእግዚአብሔር አይደለም።
ኃጢአተኞችን ሊያድን: ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣበት ዋና ነገር ኃጢአተኞችን ሊያድን ነው።
በአዳም በደል ምክንያት ዓለም ሁሉ ኃጢአተኛ በመሆኑ የእግዚአብሔር ፍርድ አለበት። በዚህ ምክንያት
ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ፍርድ ተሸክሞ በመስቀል ላይ ሞተ። ዮሐንስ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም
ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ አለሙን እንዲሁ
ወዶአልና” ይላል (ዮሐ 3፡16)። ስለዚህ ዓለም የዳነው እንዲሁ እግዚአብሔር ስለወደደው እንጂ የሙሴን ሕግ
ስለፈጸመ አይደለም ይህም ጸጋ ይባላል። ክርስቶስም በሕግ ላይ የተመሠረተውን ኪዳን ሳይሆን በራሱ ደም
የተመሠረተውን ኪዳን ሠጥቶናል (ማቴ 26፡27)። ኃጢአተኞች በእግዚአብሔር ጸጋ እንጂ በሙሴ ሕግ ሊድኑ
አይችሉም። ጳውሎስ ለአንድ ሰዓት እንኳ ሳይለቀው ጸንቶ የቆመበት የወንጌል እውነት ይህ ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ የነቢያትን አገልግሎት ወርሶ ነቢይ መሆኑ (የሐዋ 3፡22)።
የዳዊትን ዙፋን ወርሶ ንጉሠ ነገሥት መሆኑ (ሉቃ 1፡35)።
የአሮንን ክህነት ወርሶ በመልከጸዴቅ ምሳሌ ለዘለዓለም ሊቀ ካህናት መሆኑ (ዕብ 7፡1-8፤ 8፡13)። የወንጌል
እውነት ነው።
በሞቱ ሞትን ካጠፋ በኋላ ከመቃብር ተነሥቶ ማረጉ በአብ ቀኝ መቀመጡ እና ዳግም ለፍርድ የሚመጣ መሆኑ
የወንጌል እውነት ነው።
ይህ እውነት በሐሰተኛ አስተማሪዎች እንዳይጣመም ጳውሎስ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጓል ተደብድቧል፤
ተገርፏል፤ ተርቧል፤ ተጠምቷል፤ ተስዷል በያዘው እውነት ላይ ዋጋ ከፍሏል። ውንጌልን ከግዝረት እና
ከሌሎች ሕጎች ጋር ቀላቅለው ሊሰብኩ የሚወዱ ፈሪሳውያንን በጽናቱ አሸንፏል። ጌታ ከፈሪሳውያን እርሾ
ተጠበቁ ያለው ከትምህርታቸው ተጠንቀቁ ለማለት ነበር (ማቴ 16፡5-12)።
እኛም ከፈሪሳውያን ትምህርት አስተሳሰብ እና ፍልስፍና መጠንቀቅ አለብን። በዚህ ዘመንም ክርስቲያን
የሚመስሉ ፈሪሳውያን ሊኖሩ ይችላሉ።እነርሱንም ለይቶ ለማወቅ ከባድ አይደለም ግዝረትን እና ሌሎች ልዩ
ልዩ ኦሪታዊ የሆኑ የሥጋ ሥርዓቶችን ከወንጌል ጋር ቀላቅለው ሲሰብኩ መስማት ይቻላል። እነዚህ አደገኛ
ሐሰተኞች በመሆናቸው በትምህርታቸው እንዳንወሰድ መጠንቀቅ አለብን። የወንጌልን እውነት ያልተረዱ
የዋሃን የሆኑትን ግን ለማስረዳት መሞከር እንጂ መሸሽ ወይም ማሳደድ የለብንም። ይህ ማሳደድ የወንጌል
እውነት አይደለም።
ጸንተን እንቁም!!
በወንጌል ማፈር የለብንም ልንሰደድ፤ ልንገረፍ፤ እንችላለን ነገር ግን ያመንበት ወንጌል እውነት እና ንጹሕ
ስለሆነ ልንሸቃቅጠው አይገባንም። ልንናገረው የማንችል ከሆነ ዝም ማለት ይሻላል እንጂ የሚደርስብንን
የዓለም ተጽእኖ በመፍራት እውነት ያለሆነ ነገር ብንቀላቅልበት ከባድ ቅጣት የጠብቀናል። ጌታ እንክርዳዱን
ከስዴው ለይቶ ወደ እሳት እንደሚጥለው የተናገረውን ቃል መርሳት የለብንም። (ማቴ 13፡40)።
ሌላው የወንጌል እውነት: ሌላው የወንጌል እውነት ሰላም ደስታ ፍቅር ቅድስና ምህረት እና ጽድቅ ወዘተ
የመሳሰለው ነው። እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን በጸጋው ያዳናቸው በኃጢአታቸው ጸንተው እንዲኖሩ
አይደለም። ከኃጢአታቸው ተላቀው የጽድቅ እና የቅድስና ኑሮ እንዲኖሩ ነው እንጂ።
የእግዚአብሔር ጸጋ ኃጢአተኝነትን የሚያስወግድ እንጂ ልቅነትን የሚያበረታታ የሥጋን ኑሮ የሚያመቻች ልዩ
ፈቃድ አይደለም።
ሐዋርያው ጳውሎስ ስለእግዚአብሔር ጸጋ ሲናገር “ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጧልና
ይህም ጸጋ ኃጢአተኝነትን እና ዓለማዊ ምኞትን ክደን የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን
የአምላካችንንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን እራሳችንን በመግዛትና
በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል” ይላል (ቲቶ 2፡11-13)። እራስን
መግዛት፤ የጽድቅን ኑሮ መኖር እንዲሁም እግዚአብሔርን መምሰል የወንጌል እውነት ነው።
ወንጌል የሚባለው የክርስቶስ ሕይወት ነው በሌላ አነጋገር ክርስቶስ በምድር ላይ የኖረው ኑሮ ወንጌል ነው።
ይህን እውነት በጥሩ አነጋገር መናገር ይቻል ይሆናል የምንናገረውን የማንኖረው ከሆነ ግን እኛን የሚሰሙ
ሰዎች በወንጌል እውነት ጸንተው ሊኖሩ አይችሉም።
ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም ሊታይ ይፈልጋል እኛ ክርስቲያኖች ግን የወንጌልን እውነት ባለሞኖር ግርዶሽ መሆን
የለብንም። እግዚአብሔር የገለጠውን እውነት፤ መንገድ ሕይወት የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የጋረዱ ሁሉ
ወዮላቸው። ኃጢአተኝነት እና ዓለማዊ ምኞት ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወታችን እንዳይገለጥ የሚከለክል
ግርዶሽ ነው።
በእኛ እና በዓለም መካከል ልዩነት መኖር አለበት ይህም ሊሆን የሚችለው በወንጌል እውነት ጸንተን ስንኖር
ነው። የጽድቅ እና የቅድስና ኑሮ ከዓለም የምንለይበት ዋና ነገር ነው። አለባለዚያ ኢየሱስን እወቁ የሚለው
ስብከታችን ባዶ ጩኸት ሆኖ ይቀራል።
“በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት
የሚገባ አይደለም” ይላል (ማቴ 7፡21)። ይህም የወንጌል እውነት ነው። ትክክለኛውን እረፍት የምናገኘው
የእግዚአብሔርን ፈቃድ ስናደርግ ነው። የእግዚአብሔር ፈቃድ መቀደሳችን ነው ያለ ቅድስና እግዚአብሔርን
ማየት እንደማንችል ተጽፏል “ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና የእግዚአብሔር
ጸጋ ለማንም እንዳይጎድለው” ይላል (ዕብ 12፡14)። ልባችንን ለእግዚአብሔር እንስጠው ይህ ማለት በወንጌል
እውነት ጸንተን ለመቆም እንወስን ማለት ነው።
አለቆች የመሰሉት ግን በፊት ማን እንደነበሩ አይገደኝም እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ አያዳላም
አለቆች የመሰሉት አንዳች እንኳ አልጨመሩልኝምና (ቁ. 6) (... ይቀጥላል)

No comments:

Post a Comment