Saturday, February 26, 2011

KING ( ያልፋል ከዲያቆን አሸናፊ መኮንን)


ያልፋል
                                       
ሰውዬው ምንም ቢደርስበት “ይህም ያልፋል” በማለት የሚጽናና ነበር በዚህ ምክንያት ስሙ “ይህም ያልፋል” ሆነ።  ይህ ሰው ኮት አፋፍ ላይ ደርሶ ሲያጣጥር ሳለ ወዳጆቹን ጠርቶ በመቃብሬ ላይ “ይህም ያልፋል” ብላችሁ ጻፉ በማለት ተናዘዘ።  እነርሱ ግን በጣም ተበሳጭተው “አላበዛኸውም ደግሞ ኪዚህ በኋላ ምንድነው የሚያልፈው?” አሉት።  ያ ሰውም ሞተ።  እነርሱም ቃሉን ለማክበር በመቃብሩ ድንጋይ ላይ “ይህም ያልፋል” ብለው ጻፉ።  ለካ በመቃብሩ ላይ መንገድ ያልፍ ኖሯል መቃብሩ በወሩ ፈጸ።  እነዚያ ሰዎችም እውነት ነው “ሁሉም ያልፋል” ብለው ተገረሙ።

ትውልድ አልፎ ትውልድ ተተካ።  ያለፉት የነበሩ አይመስልም።  ያሉትም የሚያልፉ አይመስልም።  ግን ቋሚ እግዚአብሔር ብቻ ሆኖ ሀሉን ያሳልፋል።  ብዙ ቆንጆዎች ረገፉ ውበት ሐሰት ደም ግባትም ከንቱ ነው የሰው ብርቱ የለውምና ብዙ ጀግኖች ሞቱ።  የነገስታት ክብር መቃብር ገዛው።  ፈላስፋዎች ሊቃውንቶች ስማቸው ብቻ ቀረ።  ጽዋ በሚዞርበት ዓለም በዙረቱ ስንቶች ደኸዩ ስንቶች ከበሩ!

በአንድ ሰርግ ላይ ሰባኪው ስለይቅርታ በአጽንዖት ሲያስተምር አንድ ሰው “ይቅር አልልም ቂም አይበሰብስም”  በማለት በድፍረት ሲናገር ሰምቻለሁ።  ዛሬ መሸነፍ መስሎን ይቅርታን ብንጠላም ቂምና በቀላችን የዛሬውን ስሜታችንን ያልፋል እንኳን ቂማችን እኛም እናልፋለን።  ሁሉም ሲያልፍ ይቅርታን መናፈቃችን አይቀርም።  ይህ ግን ነፍስን ለመጨበጥ እንደመሮጥ ነው።

በየመቃብሩ ይቅር በለኝ እያሉ መራራ ለቅሶ የሚያለቅሱ በአደባባይ በደላቸውን የሚናዘዙ በታለቅ ፀፀት የሚጮሁ ወገኖች ብዙ ናቸው።  ያ የጠሉት ሰው የሚሞት ስላልመሰላቸው ብዙ በደል አድርሰውበታል ወይም ይቅርታ ነፍገውታል።  በሞት ማለፍ የመጣ ቀን ግን የልመሰላቸው ነገር ሆኗልና ሰማይ ይጫናለቸዋል።  ከሰውዬው በደል በላይ የራሳቸው በደል ይታያቸዋል።  አይመለስምና መካስ አለመቻላቸው አይገኝምና አብረው መኖር አለመቻላቸው ያንገበግባቸዋል።  በእውነት ሁሉም ያልፋል።

አንዲት እናት ቤታቸው ለዘመናት ሰላም አጥቶ ሦስት ልጆች በተከታታይ ቀበሩ።  አራተኛዋ ልጅ ስትሞት በልቅሶ መሐል ተነሥተው የሞተችው የእኔ ልጅ ናት አታልቅሱብኝ ከእነዚያ ጋር ስንባላ በሞት አለፉ።  አሁንም አልተማርንም ነበርና ይህች የደረሰች ልጄ ሞተች።  ወገኖቼ “የቆመው ሳይዋደድ ለሞተው መናደድ” ምን ይጠቅማል?  ብለው እርቅ ወረደ።  አልቃሿ በቆመችበት ቦታ ሆና ስህተት የመሰላትን ትነቅፋለች::

“ምን ዘመን መጣብን ዘመነ መጋኛ
የታቀመመው አይድን ያለው አይስማማ”

ይህች አልቃሽ ሲሰገድላቸው የነበሩትን ንጉስ አውርዶ ለአብዮቱ ይጨፍርየነበረውን ወገን እነዲህ ብላ ገስጻዋለች፡-

“ዓለም ዋሾ ዓለም ወላዋይ
ከጃንሆይ ግቢ አልነበርሽም ወይ”

ሲያልፍ ሀሉም ነገር ይሰማናል።  ልናየው የጠላነው ሰው ሲርቅ ያባባናል።  ለሞት የተመኘነው ሲሞት ያስደነግጠናል።  ሙት አይወቀስም ብለን በክፉ እንኳ አናነሳውም በእውነት እንዲህ የሚያጨካክነን ዘላለም የምነኖር ስለሚመስለን ነው።  በሙሉ ልብ የሚያቆመን ይቅርታ እንጂ የዛሬው ጠንካራ ልብ አይደለም።  የናድነው ትዳር ያፈረስነው ባልንጀርነት የበጠስነው ፍቅር መነሻው መልካም እንደነበር ስናስብ ትዝታው ዕረፍት ይነሳናል።  ለወደፊቱ ከምናስቀምጠው በረከት ነው።  ይህችን ዓለም ለቀን ልንሄድ ስንል ሕይወትን ወደኋላ መልሰን ማየት ትርፉና ኪሣራችንን መተሳሰባችን አይቀርም።  ያን ቀን በዚህ ምድር ላይ ማንንም ለመጥላት አልኖርኩም ብለን ለራሳችን መናገር ስንችል ብቻ ሞትን በደስታ እንጋፈጣለን።

በሞትን ጊዜ ቂምና በቀላችን አብሮ ይቀበራል።  ሁሉም ነገር ይቀራል።  ዛሬ ከሰው ጋር የምንጣላው ስማችንን ስላጠፉት ነው።  ከሞትን ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ግን “አስከሬኑ ታጠበ?” እንጂ “እገሌ ታጠበ?” አይሉንም።  ዕድሜ ልካችንን የኖርንለት ስማችን በጥቂት ደቂቃ ይጠፋል።  ለገንዘብ ስንል ወንድማችንን ለሞት እንመኘዋለን።  ነገር ግን ከሰበሰብነው ሀብት አእዱም ሳይከተለን ዓለምን ወደኋላ እምነትን ከፊት አድርገን እንጓዛለን።  የሰበሰብነው ንብረትም ለማናውቀውና ለማንፈልገው ሰው ይሆናል።  በእውነት ይህች ዕድሜያችን እንኳን ለጠብ ለፍቅርም አትበቃም።

አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፡- ምንም ቢበድልህ የወንድምህን ሞቱን አትመኝ።  እርሱ ሞቶ አንተ አትቀርምና።  አንድ አባትም “ሟችም ገዳይም ሁለቱም ሟቾች ናቸው።  የቅደም ተከተል ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡

መሾምም መሻርም መከበርም መዋረድም መታመምም መወፈስም ማዘንም መደሰትም መታሰርም ነጻ መሆንም ማሸነፍም ማግኘትም ማጣትም መክነፍም መቀዝቀዝም ማበድም መረጋጋትም መወደድም መጠላትም መተኛትም መንቃትም መቀየምም መበቀልም ሁሉም ያለፋሉ።  በዚህ ወራጅ የሚል ድምፅ በበዛበት ዓለም የሚያረካን ነገር ቢኖር እግዚአብሔር ማለፍን ትልቅ ጸጋ አድርጎ መስጠቱ ነው።  ማለፍ ባይኖር የረገጠ ደስ እንዳለው የተረገጠ እንደከፋው በቀረ ነበር።  የበደል ንስሓ የሚገባው የተበደለ ለምስጋና የሚበቃው የማለፍ ሥርዓትን በሚሰራው በእግዚአብሔር ነው።  ይህንን ካየን የይቅርታ ሰው ለመሆን  የሚረዱንን ባሕርያት እናያለን።

ይቆየን
ወደፊት የተቀያሚ ሰዎች ባሕርይ ብልን እንመለከታለን

No comments:

Post a Comment