Wednesday, February 16, 2011

አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያሪክ(የሻለቃ ጌታቸው የሮም )



አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያሪክ

የታሪክ ማስታወሻ ከሚለው የሻለቃ ጌታቸው የሮም መጽሃፍ የተወሰደ 
የለውጥ ረመጥ ታሪክ::                                                           

የኢትዮጵያ ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በኢትዮጵያ ሁለተኛ ፓትርያሪክ ናቸው።  ፓትርያሪክ ባስልዮስ እስኪሞቱ ድረስ በምክትልነት ከዚሁም ሥልጣናቸው ላይ የሐረርጌ ክፍለሃገር ጳጳስ በመሆን እንደራሴያቸውን ሐረር ውስጥ አስቀምጠው ሠርተዋል።  የአቡነ ቴዎፍሎስ የዚህ ስልጣን ባለቤት መሆናቸው እንደሚያስረዳው ፓትርያሪክ ባስልዮስ አርፈው በምትካቸው ስለተመረጡ ነው።

የ፲፱፻፰፮ ዓ.ም በኢተዮጵያ ወስጥ በመካሄድ ላይ በነበረው ለውጥ ላይ ምንም ዓይነት ተቃውሞ ሳያሳዩ በኢትዮጵያ አስተዳደር ታሪክ ወስጥ ቤተ ክህነትን የሚያሠጋና የአስተዳደሩም መሣሪያ መሆኑን በተገነዘቡ መኮንኖች ውሳኔ መሠረት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎሰስ ተይዘው እንዲታሰሩ ተደረገ።  እርምጃው በሳቸው ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ጳጳሶች ካህኖች መሪጌታዎች እያታደኑ ወደወህኒ ቤት የተላኩበት ጊዜ ነበር፡፡

ፓትርያሪኩ ግን የታሰሩበት የተገለለ ቦታ በጃንሜዳ በክቡር ዘበኛ ቅጥር ግቢ ውስጥ በክብር ዘበኛ ቁጥጥር ሥር ነበር።  በዚህም እስር ቤት ረዘም ላሉ ወራት ቆይተዋል በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳሉ ባልታወቀ ምክንያት ከታሰሩበት እስር ቤት በመጥፋታቸው በደርጉ ቤተ መነዕግሥት ውስጥ ጭንቀት ተፈጥሮ ነበር።

ይህንን አስመልክቶ ያጋጠመኝን መግለጽ እፈልጋለሁ።  እኔና የሥራ ጓደኛዬ ቢሮ ተቀምጠን ስለ ስራ ጉዳይ በመወያየት ላይ እንዳለን ከጥዋት አራት ሰዓት ሌ/ኰ ዳንኤል አስፋው ስልክ ደውሎ የሥራ ጓደኛዬን አነጋገረው።  ዳንኤልም ሲናገር አብዮታችን ካጋጠመን ሁኔታዎች ወስጥ እንደዛሬ ጉድ ሆነን አናውቅም፣ ያ የማይረባ ቄስ ከታሰረበት ጠፍቷል።  ወዴት እንደሄደ አናውቅምና እናንተም በፍለጋው ተባበሩን አለ።  የሥራ ጓደኛዬም የጠፋው ማን እንደሆነ ስላልገባው ዳንኤልን ጠየቀው ፓትርያርኩ ነዋ አለ።  ቀጥሎም አገሩ ጎጃም ስለሆነ ወደዚያው ሊሔድ ይችላል።  በሔሊኮፕተር ወይም በትንሽ አውሮፕላን ካገር ሊወጣ ይችላል ብለን ስለምንገምት የትበቃ ቦታዎችን ሀሉ አጠናክሩ አለ።

የሥራ ጓደኛዬም የኔን ስም ጠራና አብረን በመሆን ወደ ጎጃም አቅጣጫ ጥበቃውን እናጠናክራለን፤ ለበር ጠባቂዎችና ለአውራጃዎች ትዕዛዝ እናስተላልፋለን አለውና ስልኩን ዘጋ።

የሥራ ጓደኛየም ሁኔታውን ነገረኛና ሁለታችንም ለተወሰነ ደቂቃ ፀጥ ብለን ማሰብ ጀመርን።  ትንሽም ቆይተን ሣናስበው በአንድ ጊዜ ለመናገር ሞከርን።  ተሳሳቅንና ሁኔታው በመረጃ ሠራተኞች በኩል ለክፍሎች እንዲተላለፍ አድርገን እኔና እሱ በኔ ነጅነት በቮልስዋገን መኪና በጐጃም በር በእንጦጦ በኩል ጉዞ ቀጠልን።  በመኪናችን ውስጥ ራዲዮ ስለ ነበረን በአጠቃላይ ስለሚደረገው ፍለጋ ያለውን እንቅስቃሴ እንቆጣጠራለን።  ዳንኤልም የሚሰጠውን ትዕዛዝ እንሰማለን።

የፓትሪያርኩ መጥፋት የምንደግፈው ስለነበረ በጐጃም አቅጣጫ የሚደረገው ፍለጋ በሬድዮ እንዲተላለፍ አላደረግንም፤ ነገር ግን ፍቼ፣ ገብረ ጉራቻ፣ ጐሐጽዮን፣ በተባሉት ከተሞች እየደረስን በዕለት ሁኔታ በመመዝገብ አባሎች ፍለጋውን እንዲቀጥሉ ካደረግን በኋላ በዚያው አካባቢ ስንዝናና ዋልን።  ከሰዓት በኋላ ዘጠኝ ሰዓት ከዳንኤል ጋር ለመነጋገር ሬድዮ ከፍተን ጥሪ ስአደርግ በደስታ ተውጦ ያቀጣፊ ቄስ አረፋ አስደፍቀን ያዝነው እዚሁ በአዲስ አበባ ጐፋ ሠፈር እራሱ በሠራው ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሸጉጦ ባሳደገው በራሱ አሽከር ጥቆማ ተያዘ ስለተባበራችሁን አመሰግናለሁ አለና ራዲዮኑን ዘጋው።

በፓትያሪኩ መያዝ እኛ ብቻ አይደለንም የተበሳጨ ነው።  አያሌ ወታደራዊና የሲቪል አባሎችን ሀሉ አሳዝኗል።  ክገማሽ ሰዓት በኋላ ዳንኤል በድጋሚ ደወለ፡፡  የደወለበትም ምክንያት በአንቦ አውራጃ ሸፍተው የነበሩት ሰዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ቸግሮናልና ለመወያየት በደንብ የሚያስረዳ አንድ መኰንን ላኩልን አለ።  እኔ ሬሴ ጉዳዩን ለማስረዳት ቤተ መንግሥት ዳንኤል ቢሮ ገብቸ ሰላምታ ሰጠሁት።  እሱም ከሌሎቹ መኰንኖች ጋር ጸብ ፈጥሮ ይጨቃጨቃል።

ጉዳዩን ከጨረሰ በኋላ ቀና ብሎ አይቶኝ ብዙም አላነጋገረኝም።  በቀጥታ የተጠራሁበትን ምክንያት ማብራራት ጀመረ።  ስለሚፈልግ ጉዳይ ግን በኛ በኩል የሚታወቅ አልነበረም  ወድያውኑ ሻለቃ ዮሐንስ የሚባለውን ስልክ ደውሎ ካነጋገረ በኋላ ጉዳዩ በደርጉ ምርመራ ክፍለ ውስጥ የተያዘ ነው።  ዳንኤል እኔን ቀና ብሎ ካየኝ በኋላ ይህ ጉዳይ በኛ በኩል የሚፈፀም ይመስለኛል መሄድ ትችላለህ አለኝ።  እኔመዕ ከዳንኤል ቢሮ ወጣሁና ሻለቃ ዮሐንስ ከተባለው የደርጉ መርመራ ክፍል ሹም ጋር ለመገናኘት ገባሁ።  ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ዳንኤል ዳንኤል ለምን እንደጠራኝ ነገርኩት።  ዮሐንስም የሚሰራውን አያውቅም ብሎኝ ባሌላ ጉዳዮች ላይ አውርተን ወደ ቢሮዬ ተመለስኩ  ሻለቃ ዮሐንስ ሌ/ኰ ዳንኤልን የገደለው ነው።

ስለፓተሪያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ ጉዳይ ለሻለቃ ዮሐንሰዕ ስናደርግ የዋልነውን ፍለጋ አስረድቸው ነበር።  እሱም በጣም ተናደደ።  ከኔም ሆነ ከዳንኤል የተሻለ ጉዳዩን ያውቀዋል።  ዮሐንስም እንዲህ አለ << ያዋረዱት እራሳቸውን ሳይሆን ሁላችንንም ነው፤ እንደደረስንበት ከሆነ መውጣት ይችሉ ነበር።  አሁን የዳንኤል መጫወቻ ሆኑ።  በባዶ እግራቸው እንዲሄዱ አድርጓቸዋል፣ ጸጉራቸው ተላጭቷል፣ ቁምጣ አስለብሷቸዋል፣ እጃቸውንና እግራቸውን አጣምሮ አስሯቸዋል፣ ወደፊትም ሊገላቸው ይችላል!>> አለና ስሜቱን ገለጠልኝ።  በኋላ ሌላ እንደምንገናኝ አድርገን በሄድኩበት አኳኋን ቤተ መንግሥቱን ለቅቄ ወጣሁ።

የፓትርያሪኩ ጣጣ በሳቸው ብቻ አላበቃም።  በጠፋበት እለት የነበሩ የጥበቃ ዘቦች ሁሉ ታስረው እየተሰቃዩ ነው።  ከሳቸው መጥፋት ጋር ተባብረዋል የተባሉ ሰዎች በሙሉ በምጢር እየተጠለፉ የት እንደደረሱ አልታወቀም።  መጨረሻው አልታወቀም እንጅ ሊያወጣቸው ነበር ተብሏል የተጠረጠሩ ብዙ ድርጅቶችና ሰዎች ነበሩ ተብሎ ምርመራው ቀጥሎ ነበር።

ከዚህ በኋላ ለጥቂት ዓመታት በቤተ መንግሥቱ እስር ቤት ውስጥ ታስረው ከቆዩ በኋላ ከብዙ የቀደሙ ባለሥልጣኖች ጋር የት እንደደረሱ እስካሁን አልታወቀም።  ስለዚህ የነ ሌ/ኰ መንግሥቱ የጭካኔ እርምጃ በቤተ ክርስቲያን መሪዎችም ላይ ይኸንን ይመስል ነበር።  የፓትርያርኩ መጥፋትና በኋላም መያዝ ትክክለኛው ሁኔታ ይህን ነው።  ይህንንም ለማብራራት የፈለግሁበት ብዙ ሰዎች በተለያየ ትርጉም የፓትርያርኩን ሁኔታ ስለሚገልፁት ተጨባጩን ሁኔታ ለማወቅ ለሚፈልጉ ሁሉ በቦታውና በስራው ላይ ተሰማርቸ ያየሁትን ለመግለጽ ያህል ነው።

No comments:

Post a Comment