የስደተኛ ወላጅ ልዩ አደራ
ከአሜሪካ ቀደምት ሰፋሪዎቸ ቀጥሎ አይሪሾች እስራኤላውያን (ጁዊሽ) ሕንዶች እና ቻይናዎች ባህር አቋርጠው ወደ ምድረ አሜሪካ የተሰደዱ መጤዎች ናቸው። ቀደም ብለው የመጡት ወላጆቻቸው አሁን አሁን የሉም ወይመ በጣም አርጅተዋል። ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ግን እስራኤላዊ ማንነታቸውን ሳይለቁ አሜሪካዊ ሆነዋል ሕንድነታቸውን ሳይለቁ አሜሪካዊ ናቸው። ቻይናዊ ቋንቋቸውን እና ባሕላቸውን ሳይተዉ ፍጹም አሜሪካውያን ናቸው።
የኛ ልጆችስ እንዴት ይሆኑ ይሆን? ኢትዮጵያዊ ልጆቻችን ማንነታቸውን እንደያዙ አሜሪካዊ ይሆናሉ ወይስ በታሪክ አጋጣሚ በግዞት ወደ አሜሪካ መጥተው ማንነታቸውን ማግኘት እስካይችሉ ድረስ ከወገናቸው እንደተነጠሉት አፍሪካ-አሜሪካውያን አዲስ ማንነት ፍለጋ ይባክናሉ? ወይስ በዓይናችን ፊተ እያደጉ ያሉት ልጆቻችን በኢትዮጵያዊ ማንነታቸው በኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖታቸው ላይ መልካሙን አሜሪካዊ እሴት ይገነባሉ ወይስ ከሃብትና ሀገር በስተቀር ይሄ ነው የሚባል ሃይማኖታዊ መሰረት ካልወረሰው ግብረሰዶማዊነት እንደ መብት ክህደትን እንደ ሳይንስ እምነትን እንደ ፋሽን ዝሙትን እንደ ነጻነተ ከሚቆጥረው ከንቱ የፈረንጅ ክፍል ጋር ይቀላቀላሉ?
ይህ እንዳይሆን ማድረግ የስደተኛ ወላጅ አደራ ነው።
ዘረ ኢትዮጵያውያን በሰሜን አሜሪካ ከአንድ ትውልድ የዘለለ እድሜ አላስቆጠርንም። ፈተናው ግን ቀድሞን አሜሪካ ገብቷል። አይሪሾች አልፈውታል ጁዊሺች አልፈውታል ህንዶችና ቻይናዎች እያለፉት ነው።
የኢትዮጵያዊነት መልካም እሴትና የቀና ሃይማኖት ጠብቆ አሜሪካዊ እሴትን የመዋኃድ ዓላማን ለማሳካት የስደት ዓለም የሚያስከፍለውን ዋጋ ሁሉ እየከፈሉ ልጆቻቸውን በማሳደግ ላይ ያሉ ወላጆች የተለየ ቦታ አላቸው።
ከሁሉ በላይ ደግሞ ልጆቻቸው ጥሩ ቦታ እንዲውሉ የተሻለ ትምህርት ቤት እንዲማሩ ስነ ልቦናቸው እንዳይጎዳ ወዘተ… ሲሉ የማይለመድ የሚመስለውን የኑሮ ዘይቤ ሀሉ ለምደው የሚኖሩ ወላጆች መስዋዕትነታቸው ከባድ ነው። ፍሬ ግን የሚያፈራው እነርሱም እግዚአብሔርን ሲፈሩ ልጆቻቸውንም በዚህ መሰረት ላይ ሲገቡ ነው። ይስሃቅ የመሰለ ልጅ ለማግኘት አብርሃምን መምሰል ያስፈልጋል።
መጀመሪያውኑ ልጆችን ለወላጆች በአደራ የሰጠ ራሱ እግዚአብሔር ነው ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸውና” መዝ 126፡3። ለወላጅ ዕድሜ ሰጥቶ ለልጆች ጠባቂ መልዐክ መድቦ የሚያኖረው እግዚአብሔር ነው።
የኦርቶዶክሳው ወላጅ የመጀመሪያ አደራ ልጆቹን ቤተ ክርስቲያን ማምጣት ነው። አምጥቶ ጌም እንዲጫወቱና ሙዚቃ እንዲሰሙ መተው አይደለም እንደአቅማቸው ለጥቂት ደቂቃ የቤተ ክርስቲያንን ጣዕም እንዲለዩ ማድረግ እንጂ። እጣኑን እንዲያሸቱ ቃጭሉን እንዲሰሙ ጠበሉን እንዲጠጡ ቄሳቸውን ጳጳሳቸውን እንዲያውቁ የማንነታቸውን መሰረት እንዲያውቁ። ልጆን በሚሄድበት መንገድ ምራው በሸመገለ ጊዜ ከእርሱ ፈቅቅ አይልም። ምሳ22፡6
ወስበሐት ለእግዚአብሔር።
No comments:
Post a Comment