Thursday, January 27, 2011

KING (ነጻነት(ክፍል1) መምህር ተከስተ ጫኔ)

ነጻነት
ነጻነት የሰው ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የሰው ተፈጥሮውም ነው። እግዚአብሔር በነጻነት ውስጥ ያስቀመጠው ታላቅ ምሥጢር አለ። ይህ የእግዚአብሔር ጥበብ እጅግ
በጣም አስደናቂ ነው። ማነኛውም የሰው ልጅ እውቀትና ችሎታ በሥራ ላይ ውለው ለሰው ጥቅም የሚሰጡት በዚህ በነጻነት ምሥጢር ነው።
ነጻነት በእግዚአብሔር መንፈስ የተሰጠ የሰው ማንነት ነው። ሰው ነጻ ፍጡር መሆኑን የሚያንጸባርቀው ገና ሲወለድ ጀምሮ ነው። ሕጻናት አቅም ካላነሳቸው በቀር
ዝም ብለው ምቀመጥ አይችሉም መሮጥ መጫወት ይፈልጋሉ እናት እና አባት እነርሱን ለመቆጣጠር ሲሞክሩ ተቃውሞአቸውን በለቅሶ ይገልጣሉ። ይህ ሁኔታ የነጻነት
ፍላጎት በትምህርት ወይም በአካባቢ ሁኔታ የሚገኝ ሳይሆን በተፈጥሮ በውስጣችን ያለ የእግዚአብሔር ምሥጢር መሆኑን የሚያመለክት ነው።
በዓለም ላይ ታላላቅ የርስ በርስ ጦርነቶች ተደርገዋል ፤ በየጊዜው የብዙ ሕዝብ ደም ብዙ ጊዜ ፈሶአል እየፈሰሰም ነው የሕዝብ አመጽ በየሀገሩ ይካሔዳል አብዛኛው
ምክንያት ግን ነጻነት ነው።
ነጻነትን በጣም የሚፈሩ ሰዎች ብዙ አፈና ሲያደርጉ እየነኩ ውይም እያበላሹ ያሉት የእግዚአብሔርን ምሥጢር ወይም የሰውን ዋና ነገር ሞሆኑን አይገንዘቡም።
አምባ ገነኖች መጨረሻቸው ሳያምር የቀረው የነጻነትን ምሥጢር ሳያውቁ በመቅረታቸው ነው።
ነጻነት ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል ፤ ነጻነት እስካሁን ድረስ ያለደም ተግኝቶ አያውቅም መንፈሳዊው ነጻነት እንኳ የተገኘው በደም ነው። ለምሳሌ ፤ እስራኤላውያን
ከፈርዖን ሁለንተናዊ አገዛዝ ነጻ የወጡት ነውር የሌለለበት በግ ታርዶ ደሙ በር ላይ ከተረጨ [ከተቀባ] በኋላ ነበር። እንዲሁም ማነኛውም ኃጢአተኛ ከበደሉ ነጻ
ሊሆን የሚችለው ስለበደሉ ያቀረበው መሥዋት ከተሠዋ በኋላ ነው።
ነጻነት እንዲሁ በዋዛ የምናወራው ነገር አይደለም ፤ በነጻነት ምክንያት በዓለም ላይ ብዙ ደም ፈሷል። ነጻነት ይህን ያህል ዋጋ የሚያስከፍል ለምን ይሆን? ብለን
ብንመረምር በሰው ውስጥ ያለ መታፈን የማይችል የእግዚአብሔር ምሥጢር ስለሆነ ነው ማለት ይቻላል።
እንግዲህ ማህበራዊ ነጻነታችንን በፖለቲካ ታጋዮች ፤ በሰባዊ መብት ተሟጋቾች በጠብመንጃ እና በራሳችን ጥረት ልናገኝ እንችላለን እውነተኛው የሕይወት ነጻነት
የሚገኘው ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ሰው የነጻነት ጥያቄው በትክክል ተመልሶለት እረፍት የሚያገኘው ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ
ሲደርስ ነው። በሰው ውስጥ ያለው የእግዚአብሔር ምስጢር ፤ ትርጉም ወይም ፍቺ የሚያገኘው ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ያልተገኘ
ነጻነት በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ ይምጣ ሌላ ባርነት አለው። በክርስቶስ ነጻ ያልወጣ ሰው ከክፉ ከገዥዎች ነጻ ቢወጣም ዛሬ እንደሚታየው ዓለም የዲያብሎስ
ባሪያ ሊሆን ይችላል። ባርነት ሙሉ ለሙሉ የሚወገደው በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው ። ይህ የእግዚአብሔር ምሥጢር ነው።
ነጻ አውጭ ነን ሲሉ የነበሩት ሁሉ ዛሬ እጃችንን በአፋችን ላይ አስጭነው እየገዙን ነው። ዲያብሎስ ዓለምን እየገዛ ያለው በባሪያዎቹ በኩል ነው። በነገራችን ላይ
በክርስቶስ ነጻ ያልወጡ ገዥዎች ዕረፍት ያመጡልናል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው። ነጻነት የእግዚአብሔር ምሥጢር ነው። ያለክርስቶስ ደግሞ ይህን ድንቅ ምሥጢር
ማወቅ መቅመስ አይቻልም።
በክርስቶስ ያለ ነጻነት
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ወደ ምድር የመጣበት እና ሥጋ ለብሶ የተገለጠበት ምክንያት ነጻ ለማውጣት ነው። ቃሉ እንዲህ ይላል።
“የጌታ መንፈስ በኔ ላይ ነው ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና ለታሠሩም መፈታትን ፤ ለእውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ
የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል” ሉቃ 4፤19።
እንግዲህ በክርስቶስ ከሦስት ነገሮች ነጻ መውጣት ይቻላል።
1.ከሠይጣን እሥራት ነጻ መውጣት ይቻላል
2.ከኃጢአት
3.በሕግ ከሚመጣ ፍርድ
ከሰይጣን እሥራት ነጻ መውጣት
ብዙ ሰዎች በሰይጣን እሥራት መያዛቸውን አያውቁም ምክንያቱም ሰይጣንን እና አሠራሩን ማስተዋል ስለማይችሉ ነው። ብዙ ጊዜ ሰይጣንን የምናውቀው በጸሎት
አማክኝነት ጮኾ ሲወጣ ብቻ ነው። በሥውር እያሰረ ፈቃዱን እንድናደርግ የሚሠራ የማይጮህ ሰይጣን መኖሩን በሚገባ አስተውለን አናውቅም ። የሰይጣንን ሓሳብ
መቃወም የምንችለው ግን ስትራቴጅውን እና አሠራሩን መገንዘብ ስንችል ነው። ጠላት በየት እና መቼ መምጣት እንደሚችል ካላወቅን ከወጥመዱ መውጣት
አንችልም ጠላትን ማጥቃት የምንችለውም የጠላትን ሁኔታ ስናውቅ ነው። ሰይጣን እኛ አንወቀው እንጂ እሱ ግን እለት እለት ይሰልለናል። በጌታችን በኢየሱስ
ክርስቶስ ብርሃን ካልኖርን ደግሞ የጨለማውን ሥራ ማወቅ እና ከዚያ የጥፋት መንገድ ማምለጥ አንችልም።
ሐዋርያው ዮሐንስ ስለኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት ሲናገር “የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ”ይላል 1ዮሐ3፥9። የድያብሎስ ሥራ
የሠራውም ሆነ ገና ያልሠራው ያለ እግዚአብሔር ልጅ ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊፈርስ አይችልም። ሐዋርያው ጳውሎስ ፤ ሰይጣን በጨለማ ውስጥ እንዴት ያኖረን
እንደነበር ሲገልጥ “በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ በነርሱም በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ
እንደሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ በፊት ተመላለሳችሁባቸው”ይላል ኤፌ2፥1
ቅ.ጳውሎስ በሰይጣን ፈቃድ የሚመላለሱትን “የማይታዘዙ ልጆች” ይላቸዋል። እንግዲህ የሰይጣን እሥራት ማለት ይህ ነው በሰይጣን ፈቃድ መመላለስ ከሁሉም
የከፋው ባርነት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ባርነት፤
_እውነት የሆነውን እንዳናውቅ
_ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ እንድንኖር
_አላማ የሌለው ባዶ ሕይወት እንድንኖር ያደርገናል።
የሰይጣን ሥውር አሠራር ሁለንተናችንን ተቆጣጥሮ የማናውቀውን ነገር እንድናደርግ ማድረግ ነው። አንዳዶችን ደግሞ “ሰይጣን የለም” በሚል ሞኝነት አሳውሯቸዋል።
ሰይጣን ራሱን ካልደበቀ ሥራውን እንደሚያስበው መሥራት ስለማይችል “ሰይጣን የለም በሚል አስተሳስብ” ራሱን ይደብቃል። በዚህ ዘዴው የሐሳብ እውርነትን
በማስፋፋት ራሱን ሳይገልጥ በጨለማ ተደብቆ በሰው ልጆች ላይ ፈቃዱን ሲፈጽም ኖሯል። ቅ.ጳውሎስ “የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው የዚህ
ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ” ይላል 2ቆሮ4፡4
ሰይጣን የሠራው ሥራ ያጠፋው ጥፋት ከጥቂት የእግዚአብሔር ሰዎች በቀር ያስተዋለው ሰው አልነበረም ። የዓለም ብርሃን የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ
ክርስቶስ በሰው ተፈጥሮ[በሥጋና በደም] ሲገለጥ ግን ማንነቱ ተገለጠ ሥራውም ፈረሰበት የሞት አደጋ የነበረባቸው ሰዎችም ነጻ ወጡ። “እርሱ ደግሞ በሞት ላይ
ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር ይኸውም ዲያብሎስ ነው በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሠሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ በሥጋና በደም
ተካፈለ” ዕብ 2፡14 እንዲል።
በሉቃስ 4፡19 ላይ“ የተጠቁትን ነጻ አወጣ ዘንድ ልኮኛል” የሚለው ቃል በሰይጣን አሠራር የአዕምሮ ጥቃት የደረሰባቸውን ፤ እውነት የሆነውን እንዳያውቁ ፤
የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዳያስተውሉ አእምሮአቸው የተያዘባቸውን ሰዎች ለማስለቀቅ መገለጡን የሚያሳይ ቃል ነው።
በሉቃስ 4፡19 ላይ“ የተጠቁትን ነጻ አወጣ ዘንድ ልኮኛል” የሚለው ቃል በሰይጣን አሠራር የአዕምሮ ጥቃት የደረሰባቸውን ፤ እውነት የሆነውን እንዳያውቁ ፤
የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዳያስተውሉ አእምሮአቸው የተያዘባቸውን ሰዎች ለማስለቀቅ መገለጡን የሚያሳይ ቃል ነው።
ዛሬም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የጠበቀ ኅብረት ከሌለን የሰይጣን ማሠሪያ ከሆነው የጨለማ አስተሳሰብ መውጣት አንችልም። የምናደርገው ሁሉ የተለመደ በመሆኑ
ብቻ እውነት ወይም ሕይወት ያለበት ሊመስለን ይችላል። ዛሬ በወንድሙ ቂም ይዞ ይቅር አልልም ማለት የተለመደ ነው። ከተለያዩ ሴቶችና ወንዶች ጋር ዝሙት
መፈጸም የተለመደ ሆኗል እንደነውር መታየቱም እየቀረ ነው። ዓለማዊነት ስግብግብግብነት ጥላቻ እና መለያየት አመጽ ሁሉ የስልጣኔ አስተሳሰብ እንድሆነ
የሚያስቡ አሉ። ርኩሰት የበዛበት ሁሉ “የሰለጠነው ዓለም ” እየተባለ ይሞካሻል።
በክርስቶስ ብርሃን ሆነን ስንመለከተው ግን ዲያብሎስ በሰው ልጆች ላይ የፈጸመው ከፍተኛ ጥቃት ወይም የርኩሳን መናፍስት ሥውር የጨለማ ሥራ መሆኑን
እናስተውላለን። ይህን ካላስተዋልን ደግሞ ከዚህ አደገኛ እሥራት ነጻ ልንወጣ አንችልም።
ኢየሱስ ክርሥቶስ ከማንኛውም የኃጢአት ሥራ ወይም የግብዝነት ኑሮ ነጻ ማውጣት ይችላል።
ኢየሱስ ክርስቶስ የሰለጠነውንም ሆነ ያልሰለጠነውን ዓልም ከአጋናንንት እሥራት ነጻ ማውጣት ይችላል። ዋናው ነገር ግን ወደ እርሱ ዘወር ማለት ነው ቃሉ እንዲህ
ይላል “ወደጌታ ግን ዘወር ባለ ጊዜ ሁሉ መጋረጃው ይወሰዳል ጌታ ግን መንፈስ ነው የጌታ መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ” 2ቆሮ 3፥16-17። በነጻነት ልንኖር
ክርስቶስ ነጻ አወጣን!!!
ይቀጥላል …..

No comments:

Post a Comment