ነጻነት (ካለፍፈው የቀጠለ) ክፍል ፯
ይህ ዘር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በዘመኑ ፍጻሜ ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለ ዘርዓ ብእሲ የተወለደው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአብርሃም
የተነገረለት ዘር ነው። የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት፤-
በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሠሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ
የመላእክትን አይደለም ዕብ 2፡15-16።
ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ ስለብዙዎች እንደሚነገር ለዘሮቹ አይልም ስለ አንድ እንደሚነገር ግን ለዘርህ ይላል እርሱም ክርስቶስ ነው ገላ
3፡16።
ስለዚህ ለአብርሃም የተነገረው ማለት የምድር ነገዶች በዘርህ ይባረካሉ የሚለው ተስፋ የተፈጸመው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው።ገላ 3፡6-10።
ኢይሱስ ክርስቶስ እንዴት ነው ያዳነን:-
የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት ለመረዳት እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውን የመሥዋእት ሥርዓት ጥቂት እንመልከት፤-
በብሉይ ኪዳን የስዎችን ኃጢአት ለማስተሥረይ በጎች መስዋእት ይሆኑ ነበር። አንድ ኃጢአተኛ በጉን ወደ ካህኑ ይዞ ይመጣና በበጉ ላይ እጁን ይጭናል
ካህኑ ከጸለየ በኋላ የሰውየውን ኃጢአት የተሸከመውን በግ አርዶ በእሳት ያቃጥለዋል። ከዚያ ኃጢአተኛው ሰው በበጉ ደም ምክንያት የኃጢአት ሥርየት
አግኝቶ በሰላም ይሄዳል።ዘሌ 4፡1-35 ያንብቡ። ደም የሚያስተሠርይበት ምክንያት ከሕይወቱ የተነሣ ነው።
የሥጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና ፤ ደሙም ከሕይወቱ የተነሣ ይስተሠርያልና ፤ በመሠዊያው ላይ ለነፍሳችሁ ማስተሥረያ ይሆን ዘንድ እኔ ለእናንተ
ሰጠሁት። እግዚአብሔር ግን በእንስሣት መስዋእት ደስ አላለውም። ምክንያቱም የእንሥሣት ደም ሥጋን እንጂ ሕሊናን ሊያነጻ አልቻለም። የሚከተሉትን
ጥቅሶች እናንብብ፤-
የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና ዕብ 10፡4
የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለኔ ምን ይጠቅመኛል? ይላል እግዚአብሔር የሚቃጠለውን የአውራ በግ መሥዋዕትን እና የፍሪዳን ስብ ጠግቤአለሁ የበሬና የበግ
ጠቦት የአውራ ፍየልም ደም ደስ አያሰኘኝም ኢሳ 1፡11።
መስዋዕትን እና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ በሙሉ በሚቃጠል መሥዋዕት እና ስለ ኃጢአት በሚሠዋ መስዋዕት ደስ አላለህም። መዝ 39፡
6-8።
ይህ ሥራዓት ዓለምን ሊያድን እና ሰውን ፈጽሞ ሊቀድስ አይችልም ዕብ 9፡10። በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ደስ አላለውም። እግዚአብሔር ደስ
ካልተሰኘ ደግሞ ሊባርከን አይችልም።
ታዲያ እግዚአብሔር በምን ደስ ሊለው ይችላል?
እግዚአብሔር ደስ የተሰኘው በአንድያ ልጁ መሆኑን እንዲህ ሲል መስክሯል።
እነሆም ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ እነሆም ድምጽ ከሰማያት መጥቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ
የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ ማቴ 2፡16-17። አብ በእርሱ ደስ ይለኛል ያለው ሰውን ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብና ፍጹም መስዋዕት እርሱ ኢየሱስ
ክርስቶስ መሆኑን ሲገልጥ ነው። ይህን ምሥክርነት የሰማው መጥምቁ ዮሐንስ በማግስቱ ኢየሱስን ወደርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ "የዓለምን ኃጢአት
የሚያሰወግድ የእግዚአብሔር በግ እነሆ" ዮሐ 1፡29።
ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን በግ ተባለ? ኃጢአተኞች እጃቸውን ጭነውበት በደላቸውን ተሸክሞ በመስቀል ላይ ስለተሠዋ ነው። ኢሳይያስ ስለታረደው በግ
እንደዚህ ይላል
ምዕራፍ 53።
1፤ የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጦአል?
2፤ በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል። መልክና ውበት የለውም፥ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም።
3፤ የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፤ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፥ እኛም አላከበርነውም።
4፤ በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው።
5፤ እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።
6፤ እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ።
7፤ ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።
8፤ በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ?
9፤ ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፥ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፥ በአፉም ተንኮል አልተገንበትም ነበር።
10፤ እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈከደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፥ ዕድሜውም ይረዝማል፥
የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል።
11፤ ከነፍሱ ድካም ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፥ ኃጢአታቸውን ይሰከማል።
12፤ ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና፤
እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።
በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ከትምህርታችን ርእስ ጋር የሚመሳሰሉትን ጥቅሶች ወስደን እንመልከት፤-
የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ እና እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ የሚሉትን ቃላት እናስተውል፤-
ተግሣጽ ማለት ቁጣ ማለት ነው። ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች እንደነበርን ያስታውሱ ኤፌ 2፡3። እንግዲህ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የሆነው መከራ ግርፋት ፤
ሥቃይ ሁሉ በኛ ላይ ሊሆን የነበረው የእግዚአብሔር ቁጣ ነው። በመስቀል በክርስቶስ ላይ የተፈጸመው ሁሉ የደኅንነታችን ቁጣ ነው። ይህ ሁሉ መከራ
በክርስቶስ ላይ ለምን ደረሰ? ብንል እግዚአብሔር የሁላችንን በደል በርሱ ላይ ስላኖረ ነው። ቁጥር 11 ላይ ጻድቅ ባሪያዬ በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል
ኃጢአታቸውንም ይሸከማል እርሱም ብዙዎችን ይወርሳል። ይላል። ቤዛ የሚለውን ቃል ከድኅነት ጋር ያለውን ግንዛቤ እንመርምር።
ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? እንደተባለ ቤዛ ምትክ የሚል ትርጉም አለው ይኸውም በአንድ ሰው ፋንታ ሌላ ተተክቶ እዳ መክፈሉን የሚያመለክት
ነው። በብሉይ ኪዳን ሥርዓት ኃጢተኛው በጉን በካህኑ ፊት ካቀረበ በኋላ እጁን ይጭንበታል እንዲህ የሚያደርገው እኔ ሞት ይገባኛል በድያለሁ ሲል በጉን
ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? እንደተባለ ቤዛ ምትክ የሚል ትርጉም አለው ይኸውም በአንድ ሰው ፋንታ ሌላ ተተክቶ እዳ መክፈሉን የሚያመለክት
ነው። በብሉይ ኪዳን ሥርዓት ኃጢተኛው በጉን በካህኑ ፊት ካቀረበ በኋላ እጁን ይጭንበታል እንዲህ የሚያደርገው እኔ ሞት ይገባኛል በድያለሁ ሲል በጉን
በራሱ ፋንታ መተካቱ ነበር። በጉም ለኃጢአተኛው ቤዛ ሆኖ ከተሰዋ በኋላ ኃጢአተኛው ነጻ ይሆናል። ኢየሱስ ክርስቶስም ልክ እንደ በጉ ለኃጢአተኞች ቤዛ
ሆኖ ስለተሰዋ ቤዛ ብዙኃን የዓለም ቤዛ ይባላል። ታዲያ ከኢሱስ ክርስቶስ ሌላ የዓለም ቤዛ የሆነ ይኖር ይሆን? የለም!!!!!!!!!!!!!!!
ቤዛ የሚለው ቃል ጥላ የሚል ትርጉም ይሰጣል። ጥላ የፀሐይን ጨረር[ቁጣ] ወይም የዝናብን እና የበረዶን ኃይል የሚከላከል የሚገድብ ነገር ነው።
እንዲሁም እኛም በኢየሱስ ክርስቶስ በማመናችን በእኛ ላይ ሊወርድ ከነበረው የኃጢት ፍርድ ዳንን። ጥላ የያዘን ሰው የፀሐይ ጨረር እንደማያገኘው ሁሉ
በኢየሱስ ክርስቶስ ያመነነን ሰውም የዘለዓለም ኩነኔ አያገኘውም። የፀሐዩ ጨረር በጥላው ላይ እንዳረፈ ሁሉ በእኛ ላይ ሊሆን የነበረው ሞትም በቤዛችን
በክስቶስ ላይ ሆኗል። ለዚህ ነው ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛ የተባለው ስሙ የተመሰገነ ይሁን አሜን!!!
ጥያቄ:- ሁለት ጥላ ባአንድ ጊዜ መያዝ ይቻላል?
ሐዋርያው ጳውሎስ ከእግዚአብሔር ቁጣ የምናመልጥበትን መንገድ እንዲህ ሲል ይገልጣል ይልቁንስ እንግዲህ በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቁጣው እንድናለን
ሮሜ 5፡10። በዚህ ትምህርት ውስጥ ልናስተውል የሚገባን የእግዚአብሔርን ፍቅር ነው። እግዚአብሔር ከመጀመሪያው አንተ ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ
የሚለውን የፍርድ ቃል ሲናገር እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል የሚለውን የማዳን ቃልም ተናግሯል። ስለዚህ ፍርዱን በመስቀል ላይ ተሸክሞልን ከሞት አዳነን።
እግዚአብሔር እራሱ የኛን በደል ተሸክሞ አዳነን እንዴት አስደናቂ ፍቅር ነው? ፍርዱ ትክክል ነው ፍቅሩም ፍጹም ነው ርኅራሔው አያልቅም ያልጠፋነው
ከእግዚአብሔር ምህረት የተነሣ ነው ተብሎ እንደተጻፈ በምሕረቱ ቤዛ ሆነልን ክብር፤ ምሥጋና አምልኮ እና ስግደት ለዘለዓለሙ ለእርሱ ይሁን አሜን!!!
እንግዲህ መዳን በሌላ በማንም የለም። ሰው መዳን የሚችለው ስለኃጢአቱ ዋጋ ሲከፍል ብቻ ነው የኃጢአት ደሞዝ ሞት ስለሆነ ሮሜ 6፡23 እግዚአብሔር
ኃጢአትን መቅጣት ባሕርዩ ነው። ነገር ግን በኃጢአት ከሚመጣ ሞት ያድነን ዘንድ የኃጢአት ዋጋ [ደሞዝን] የከፈለው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው።
ስለዚህ፤-
+ እግዚአብሔር ደስ የተሰኘበት
+ የደኅንነታችን ቁጣ ያረፈበት
+ እግዚአብሔር የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ ያኖረበት
+ ኃጢአታችንን ተሸክሞ በመስቀል የሞተ
+ ሞቶ ይተነሣ
+ ያረገ
+ በአብ ቀኝ የተቀመጠ
ማንም የለም ። መዳን የሚቻለው በርሱ ብቻ ነው።
የሚከትሉትን ጥቅሶች በቅንነት ያስተውሉ፤-
- ኢየሱስም እኔ መንገድና እውነት ፤ ሕይወትም ነኝ። በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም ዮሐ 14፡6።
- መዳንም በሌላ በማንም የለም እንድንበት ዘንድ የሚገባ ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና የሐዋ 4፡12።
- ልዩነት የለምና ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል በክርስቶስ ኢየሱስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው
ይጸድቃሉ። እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተሥረያ አድርጎ አቆመው።ሮሜ 3፡23-25።
- እንደ ሕጉም ከጥቂቶች በቀር ነገር ሁሉ በደም ይነጻል ደምም ሳይፈስ ሥርዬት የለም። ዕብ 9፡23።
- የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል 1የሐ 1፡7።
እንግዲህ ይህን ታላቅ መዳን ችላ ማለት ከባድ ቅጣት አለው። በመላእክት የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነ መተላለፍና አልመታዘዝም ሁሉ የጽድቅን ብድራት
ከተቀበለ እኛስ እንዲህ ዓይነቱን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው እንዴት እናመልጣለን? ዕብ 2፡2-3 ይላል።
የሙሴን ሕግ ያልፈጸመ ሞት ይፈረድበት እንደነበረ ሁሉ፤- ከዚህ የእግዚአብሔር መንገድ ውጭ የኃጢአት ሥርየት ለማግኘት መሞከርም ከንቱ ድካም
ከምሆንም አልፎ የእግዚአብሔርን ልጅ እንደመርገጥ ፤ የጸጋውን መንፈስ እንደማክፋፋት እና የኪዳኑን ደም እንደመናቅ ስለሚቆጠር ከባድ ቅጣት
አለው። ቃሉ እንዲህ ይላል፤-
የሙሴን ሕግ የናቀ ሰው ሁለት ወይም ሦስት ቢመሠክሩበት ያለ ርኅራኄ ይሞታል ፤ የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ ፤ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም
እንደ ርኩስ ነገር የቆጠረ ፤ የጸጋውንም መንፈስ ያክፋፋ እንዴት ይልቅ የሚብስ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል? ይላል ዕብ 10፡28-31።
No comments:
Post a Comment