Monday, January 31, 2011

KING ( እርስ በእርሳችን እንዋደድ )(ዘማሪ ናፍቆት ገበየሁ)



እርስ በእርሳችን እንዋደድ

ከተከበረበትና ዘወትር ከሚመሰገንበት የንግስና መንበር እራሱን አዋርዶ ወደ ምድር መቶ ሰው ተብሎ በተፈጠረው አካል በድንግል ማርያም ወስጥ አድሮ መወለጃ ቦታ ሳይመርጥ በበረት ተወልዶ እንደማናችንም በልጅነት አድጎ በወጣትነት ዘመኑ ህይወቱን የስብከትና የትምህርት ህይወት አድርጎ ብዙ ነገር አስተምሮን በዕለተ አርብ ደሙን አፍስሶ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እዳችንን አጥቦ ሞታችንን የገደለ እሱ ኢየሱስ ሞዓ አንበሳ ነው።

እስቲ እያንዳንዳችሁ ይሄንን ጽሁፍ የምታነቡ ሁሉ በጌታ ስም ይመጠይቃችሁ አንድ ነገር አለ።  እራሳችሁን አንድ ጥያቄ ጠይቁ? ኢየሱስን አውቀዋለሁ? ወይስ ኢየሱስን እኖረዋለሁ? ኢየሱስን ማወቅ ማለት-- ኢየሱስ የአማልክት አምላክ የቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አለምን ሊያድን እንደመጣ በከብቶች በረት ተወልዶ በዕለተ አርብ እንደተሰቀለ ሃያል እንደሆነ ፍቅር እንደሆነ ወዘተ… በአፋችን ማውራት በቻ ኢየሱስን ማወቅ ይባላል።

ኢየሱስን መኖር ማለት ግን ከላይ የተጠቀሱን ሁሉ አምኖ ጌታን መስሎ በዚህ አለም መኖር ነው።  ጌታን መስሎ በዚህ አለም መኖር ማለት።  የተራቡ እያበሉ, የተጠሙ እያጠጡ, የታረዙ እያለበሱ, የታሰሩ እየጠየቁ, ያዘኑትን እያጽናኑ, ሲበድሉን ይቅር እያልን, ሰዎችን በፍቅር አይን እንዲሁም በፍቅር ህሊና እየተመለከትን, ለነሱ በመጸለይ, ያለንን በማካፈል, ወንድሞቻችንን በመውደድ, ባለመለያየተ, እርስ በዕርስ በመከባብር, በጾም በጸሎት በመበርታት, ከክፋት በመራቅ, እራሳችንን ዝቅ በማድረግ, የሚጠሉንን በመውደድ, የሚረግሙንን በመመረቅ, የወንድሞቻችንን ሃጥያት በመሸፈን, ባለመግደል, ባለመዋሽት, ባለመስረቅ, እናት አባቶቻችንን በማክበር, ክርስትናን ለዓለም በመስበክ እንዲሁም ጌታ ያላደረጋቸውንና የማይወዳቸውን ነገሮች ሁሉ ላለማድረግ ወስነን በትግል ዓለም በፍልሚያ መኖር ነው።( በትግል ወስጥ ሁሌ ማሸነፍ የለም መውደቅ መነሳት ይበዛል ነግር ግን ከበረታን የድል ጌታ ድልን ለኛ ይሰጠንና በድል ፍልሚያችን ይጠናቀቃል ማለት ነው።)

በታለቁ ፍልሚያ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ ከቶ አይርቅም ስለዚህ ልባችን ቆርጦ ከተነሳ አሸናፊዎች ነንና አንበገርም እስቲ ሁላችንንም ሁሉንም እንኳን ማረግ ቢያቅተን የበጎ ነገር ዝርዝር አውጥተን እመኝታ ቤታችን ግርግዳው ላይ እንለጥፈው እስቲ ሁሌ ማታ ማታ እራሳችንን እንፈትን ስንት ጥሩ ነገር እንደሰራን ስንት ጌታን የሚያወርድ ነገር እንደሰራን ያን ግዜ የእምነታችን ጥንካሬ እናውቃለን።  ምን ግዜም እውነተኛ እምነት ባለበት ሁሉ እውነተኛ ታለቅ የጽድቅ ስራ አለ።  በአፍ ላይ የታተመ እምነት ግን በስራው ማንነቱ ይጋለጣል እና እባካችሁ ውለታ የዋለልንን ጌታ አንበድለው እኛ እርስ በዕርሳችን በተዋደድን ቁጥር ጌታ ይከብራል ከዛ ውጪ አጠገባችን ያለውን ወንድማችንን እየበደልን ጌታን እናከብራልን እናመለካለን የምንል ከሆነ ውሸታሞች ነን ውሽት ደሞ ሃጢያት ነው የሃጥያት ብዛት ደሞ ሞትን ትወልዳለች።

ክርስቲያኖች እስከ መቼ ነው እርስ በዕርሳችን እገሌ የእገሌ እምነት ተከታይ እገሌ የእገሌ እምነት ተከታይ እያልን ክርስቶስን ደጋግመን የምንሰቅለው።  ይብቃ አይሁድ ጌታን የሰቀሉት ይበቃል እኛ ክርስቲያኖች የንጉስ ልጆች ነን ሃይማኖት መለዋወጥ አይደለም የሚያድነው እራስን መለወጥ እንጂ ሁላችንም ያለፈወን ትተን ወደጽድቅ ህይወት እንመለስ ጌታ የኮራብንና ይመካብን ዘንድ እስከመቼ እናዋርደዋለን እስከመቼ??? በትዕግስቱ ብዛት ምህረቱ ቢበዛልን ልባችን ጌታ የለም ብሎ በጌታ ላይ እስኪገዳደር ድረስ ዝም አልነው። ሁላችንም በየጓዳችን የራሳችንን ችግር ሳንፈታ የቤተ ክርስቲያን ችግር ለመፍታት እንሯሯጣለን በሽተኛ በሽታን ሊያክም አይችልም መጀመሪያ ከበሽታው መዳን አለብን በሽታን ለማከም ወይም ለማጥፋት ከፈለግን በሁሉም የክርስትና እምነት ድርጅቶች ወስጥ ችግር አለ ለምን ይሆን  በጌታ ቤት ችግር አበክሮ የበዛው ለምንድነው ሁላችንም ክርስቲያኖች ከሆንን እርስ በዕርሳችን የምንባላው የጥቅምና የቅናት ችግር ካልሆነ በስተቀር ሁላችንም እንደስርዓታችን ጌታን እናክብረው።  ክርስቲያን ክርስቲያኑን ማሳደድ ይብቃ። 

የጌታ ልጆች ገና ብዙ ስራ ይጠበቅብናል ሌሎች ከክርስትና ውጪ ያሉ አማኞች የኛን እርስ በዕርስ መበላላት ሃሰተኛነት ጥቅመኝነት ከሩቅ ቆመው በመመለከት ሞቶ ህይወት የሰጣቸውን ኢየሱስን ሳንሰብክላቸው እርቀውን ወደሌላ ሞት ይሄደሉ ታዲያ ሊዚህ ሁሉ ነፍስ በሜዳ መቅረት ማን ይሆን ተጠያቂው ኦርቶዶክስ? ካቶሊክ? ፕሮቴስታንተ? ማነው??? እኔ ልንገራችሁ ሁላችንም ነፍሰ ገዳዮች ነን።

 ወንድሞችን ከቤተ ክረስቲያን ለማራቅ ያራሳችን የሆነ ሰነድ/ድሪቶ በመደረት በየጎራው ተከፋፍለን የራሳችንን አዚም መርዝ እንረጫለን በኛ ጨዋነት ደም የተከፈለለት ነፍስ ፍጹም ሜዳ ላይ ይቀራል እያንዳንዳችን ለወንድሞች መጥፋት እዳ አለብን።  እኔ ከማውቀውና ከምከተላት  ከኦርቶዶክስ ቤት ልነሳና የማውቀውን ልናገር።  የቤተ ክርስቲያኗ ሊቃውንት አባቶች ወንጌልን ስለሰበኩ እውነት ስለተናገሩ እንደ ጠላት እየታዩ ስም በሌላቸው ስብስቦች ስም እየተሰጣቸው ግማሾቹ በስውር እየተገደሉ ግማሾቹ በመርዝ እየተገደሉ ግማሾቹ ዛሬም ድረስ ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ወንጌል በመስበካቸው እንደ ሃጥያተኛ እየታዩ በሃሰት ይከሰሳሉ። 

የዲያቢሎስ ልጆች ከሃሰት ውጪ እውነትን አያውቁም የበረቱት አባቶች በርትተውና ጠንክረው በጽናት ዛሬም ስለ ክርስትናቸው ቆመዋል ጌታም ከብሮባቸው ስሙ ከፍ ከፍ ብሏል።  ወዳጄ ሰው ሰወን ቢያከብረው ባያከብረው ዋጋ የለውም እግዚአብሔር ብቻ አይጣልህ።  እግዚአብሔር እነዚህን አባቶች ከቤተ ክርስቲን ስላላጠፋ ዛሬም በስደቱ ዓለም ተዋህዶ በህይወት አለች ነገር ግን የፉኝት ልጆች ዛርም እንደ ቀድሞው ልክ እንደ አባታቸው እውነተኞ አባቶችን ሰኮና ለመቀጥቀጥ ያደባሉ ነገር ግን ዲያቢሎስ ከዕግራቸው በታች ስለሆነ ታላቁን ስም ይዘው ሲነሱ ድምጥማቱ ይጠፋል ከአባቶቻችን ጋር ያለው ጌታ ከሁሉም ይበልጣልና ከምድራዊው ፍርሃት አባቶቻችን ነጻ ናቸው።  ይብላኝ ሳታድጉ ያደጋችሁ ለሚመስላችሁ ወጣቶች ይብላኝ ሳትማሩ የተማራችሁ ለሚመስላችሁ ወጣቶች ቀኑ ይመሽና እንተዛዘባለን።  ምንም ቢሆን የጌታ ደም ለእናንተም ነውና የፈሰሰው እባካችሁ አባቶች በሞት ሳይጠሩ እግራቸው ላይ ወድቃችሁ ይቅርታ ጠይቁ ይህ ወንድማዊ ምክሬ ነው።  ይህቺ ቀን ታልፍና ወይኔ ይመትሉበት ቀን ይመጣል።

እንዲሁም በሌሎች የክረስትና እምነት ውስጥ ያላችሁ እባካችሁ የተዋህዶን ቤተ ክርስቲያን ለቀቅ አድግጓትና ስለራሳችሁ የእምነት ድርጅት ተጨነቁ።  ክርስቲያኖችን ክርስቲያን ለማረግ ከምትሽቀዳደሙ ያላመኑትን ያልተጠመቁትን ሰብካችሁ ወደ ክርስትና ለውጡ ያን ግዜ እውነተኛ ትባላላችሁ።  ነገር ግን ከተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምን አይነት አዚም እንደያዛችሁ ባይገባኝም ዛሬም እንደጥንቱ ይህችን ቤተ ክርስቲያን እንደ ጠላት ታሳድዷታላችሁ የሰማይ ጌታ የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ማስተዋልን ይስጣችሁ እስከዛሬም ላጠፋችሁት ጥፋት ይቅርታውን ያብዛላችሁ። 

እንግዲህ ሁላችንም እርስ በዕርሳችን እንከባበር እንዋደድ እንረዳዳ እርስ በዕርስ መበላላትና መመቀኛኘት ይብቃ።  በዓለማችን ውስጥ ዛሬም ብዙ ያላመኑ ወንጌል ያልተሰበከላቸው አሉና እነሱን ህይወት ወደሆነው ጌታ እናምጣቸው አምነውና ተጠምቀው ይድኑ ዘንድ እንትጋ። የታረሰውን ማሳ ትተን  ያልታረሰውን ማሳ እንረስ በታረሰው እርሻ ላይ እንክርዳድ ከመዝራት ጌታ ይጠብቀን።  የሰማይ አምላክ ለሁላችንም ማስተዋልን ይስጠን እርስ በዕርሳችን ስንበላላ የክረስትና ጠላቶች እንዳይውጡን አብልጠን እንጨነቅ።

ደሙን ከፍሎ በደሙ የዋጀን ጌታ በደሙ ሰላምንና ፍቅርን ያድለን

ክርስትናችንን ይጠብቅልን። 
(የሃጥያቴን ብዛት ሳትመለከት ይችን ቀን ቀድሰህ የሰጠኸኝ ጌታ ስምህ ለዘለዓለም የተባረከ ይሁን)

ይቆየን

No comments:

Post a Comment