ነጻነት (ካለፈው የቀጠለ) ክፍል ፭
ያለፈው ሳምንት ንባባችንን ያቆመነው ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥ አሁን በሕይወታችን አሥሮ ከያዘን ኃጢአት ነጻ
ያወጣል? በሚል ጥያቄ ነበር ያቆምነው። መልሱ አዎ ነጻ ያወጣል ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ "ነገር ግን ገና
ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቷልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል።" ይላል ሮሜ 5፡
8። ኢየሱስ የሞተልን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ነው። ኃጢተኛች ሲል ባሕርያችንን ለመናገር እንጂ በየጊዜው
የሰራነውን ኃጢአት ለመቁጠር አይደለም በባሕርያችን ኃጢአተኞች ነን ማለቱ ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ ሳይሞት ሊያድነን አይችልም ነበር? የሚል ጥያቄ ሊኖር ይችላል። አዎ ይችላል ነገር ግን የኃጢአት
ዋጋ መከፈል ነበረበት ምክንያቱም የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነው ሮሜ 6፡23። ይህን በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ
ተብሎ ስለተፈረደ በኃጢአት መሞት የግድ ነው። ሆኖም ሁሉ ሰው ስለኃጢአቱ ዋጋ ቢከፍል አንድም የሚድን ሰው
የለም ። ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ሁለንተና በመውረስ በመስቀል ላይ የኃጢአትን ሞት ሞተ።
አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ 2ቆሮ 5፡15። አንዱ ስለሁሉ ሞተ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ
ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ።
በዚህ ቃል ውስጥ የምናገኘው ምስጢር ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሁሉ መሞቱን እና በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ
ለኃጢአታቸው እንደሞቱ ተቆጥሮላቸዋል የሚል ነው። አንዱ ስለሁሉ ሞተ ካለ በኋላ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ ይላል።
የክርስቶስ ሞት ላመኑት ተቆጥሯል ስለዚህ ከኃጢአት ፍርድ ነጻ ናቸው። እንዲሁም አሁን የሚኖሩትም ለሞተው እና
ለተነሣው ለክርስቶስ ስለሆነ በባህርያቸው ያለውን ኃጢአት አሸንፈው የጽድቅ ኑሮ መኖር ይችላሉ። በክርስቶስ
ያመነ ሰው ለጽድቅ ካልሆነ በቀር ለኃጢአት መኖር ይከብደዋል።
በሮሜ 4፡23 ላይ ነገር ግን ተቈጠረለት የሚለው ቃል ስለ እርሱ ብቻ የተጻፈ አይደለም ስለ እኛም ነው እንጂ
ስለበደላችን አልፎ የተሰጠውን እኛን ስለማጽደቅም የተነሣውን ጌታችንን ከሙታን ባስነሳው ለምናምን ለእኛ
ይቆጠርልን ዘንድ አለው ይላል። አብርሃም እምነቱ ነበር ጽድቅ ሆኖ የተቆጠረለት ይኸዉም ከሸመገለ በኋላ ልጅ
እንደሚወልድ ሲነገረው እግዚአብሔር የሚሳነው እንደሌለ ማመኑ ነበር ዘፍ 17፡6። እኛም የክርስቶስን ሞት እና
ትንሣኤ በማመናችን ይህ እምነታችን ጽድቅ ሆኖ ተቆጥሮልናል።ስለዚህ እኛም ለኃጢአት እንደሞትን እራሳችንን
መቁጠር አለብን። እንዲሁም እናንተ ደግሞ ለኃጢአት እንደሞታችሁ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ሆናችሁ
ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደ ሆናችሁ እራሳችሁን ቁጠሩ ይላል ሮሜ 6፡11።
በኃጢአታችን የመቀጠላችን እና ያለመለወጣችን ዋና ምክንያት ክርስቶስን አለመቀበላችን ብቻ ሳይሆን ለኃጢአት
እንደሞትን እና ለእግዚአብሔር ግን ሕያዋን እንደሆንን እራሳችንን አለመቁጠራችን ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ የሁላችንን በደል ተሸክሟል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ፤ ጻድቅ እና ኃጢአት የሌለበት ነው ስለዚህ እርሱ የሞተው በበደላችን እና በኃጢአታችን
እንጂ በራሱ በደል አይደለም። እስኪ የእግዚአብሔርን እና የሰዎችን ምሥክርነት ጥቂት እንመልከት
- እነሆም ከደመናው በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት የሚል ድምጽ መጣ ማቴ 17፡5
ይህ የአብ ምሥክርነት ነው።
- እኔስ አንዲት በደል ስንኳ አላገኘሁበትም ዮሐ 18፡38 የጲላጦስ ምሥክርነት
- በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው ይህ ግን ምንም ክፋት አላዳረገም ብሎ ገሰጸው ሉቃ 23፡39-41።
- ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? ከክፉዎችም መቃብሩን
አደረጉ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም ነበር ኢሳ 53፡8-9
የኢሳይያስ ምሥክርነት ።
- እርሱም ኃጢአት አላደረገም ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም ሲሰድቡትም መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል
አልዛተም፤ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን ሰጠ ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር እርሱ ራሱ በሥጋው
ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ 1ጴጥ 2፡22-24 የጴጥሮስ ምስክርነት።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ጻድቅ ሆኖ ሳለ እንደ በደለኛ ተቆጠረ እርሱ ጻድቁ እንደበደለኛ በመቆጠሩ እኛ
በእርሱ ያመንን ግን እንደ ጻድቅ ተቆጠርን።
ይህ የሆነበት ምክንያት የሁላችንን በደል በመሸከሙ ነው።
በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕማማችንንም ተሸክሟል ...እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ ይላል
ኢሳ 53፡4-7።
እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ ... ይቀጥላል
ኢሳ 53፡4-7።
እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ ... ይቀጥላል
No comments:
Post a Comment