ነጻነት (ካለፈው የቀጠለ) ክፍል ፬
ባለፈው ሳምንት ጽሑፍ ከዘለዓለሙ የኃጢአት ፍርድ ማን ነጻ ያወጣኛል? የሚል ጥያቄ ጠይቀን ነበር ያቆምነው። ዛሬ ደግሞ መልሱን እናጠናለን።
ከኃጢአት ነጻ ማውጣት የሚችለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ብዙዎቻችን የሚያስቸግረን ሊለቀን ያልቻለ ፤ የማንወደው ነገር ሁልጊዜ የምናደርገው
ዝሙት፤ ሥካር፤ ቂም እና በቀል፤ ጥላቻ፤ ውሸት፤ ወዘተ የመሳሰለው ኃጢአት በውስጣችን እየኖረ ደስታችንን ቀምቶን ይኖራል፤ በዚህ ምክንያት መንፈሳችን
እየወቀሰን የምንሰቃይ፤ በጸሎታችን ጊዜ የምንሸማቀቅ፤ ሰይጣን ደግሞ በኃጢአታችን እየከሰሰ ሰላማችንን የነሳን ብዙዎች ነን።
በኃጢአታችን ምክንያት ነፍሳችን እረፍት ስላላገኘች ሁልጊዜ ትጨነቃለች፤ ሰው በሞተ ቁጥር የእኔ እጣ ፋንታ ምን ይሆን፤ በእግዚአብሔር ፊት እንዴት እንቆም
ይሆን? እያልን ራሳችንን የምንጠይቅ ብዙዎች ነን። አድራሻችን የት ይሆን ሲኦል ይሆን ገነት? እያልን መጨረሻችንን ያላረጋገጥን አለን። አንዳዶቻችን ደግሞ እኔ
እጅግ ኃጢአተኛ ነኝ፤ እግዚአብሔር እኔን ማየት አይፈልግም፤ በሚል የሰይጣን ድምጽ ተገፋፍተን ተስፋ የቆረጥን፤ ጨርሰን ከቤተ ክርስቲያን የጠፋን፤
ከእግዚአብሔር መሸሽ አማራጭ የሚመስለን ሰዎች አለን።
ሌሎቻችን ደግሞ የኃጢአታችን ሸከም ሲከብደን፤ ከኃጢአታችን ያመለጥን መስሎን ከሰይጣን ክስ ነጻ ለመውጣት እግዚአብሔር የለም በሚል ስሜት እረፍት
ለማግኘት የምንሞክር አንጠፋም።
ሌሎቻችን ደግሞ በሃይማኖት አባቶች በማመካኘት ከኃጢታችን ነጻ የምንሆን የሚመስለን፤ የእግዚአብሔርን ቃል ላለመስማት ጆሮአችንን የደፈንን፤ ወይም
ትክክለኛውን ሃይማኖት ስለማናውቀው ሃይማኖት አይስፈልገንም በማለት ራሳችንን የምናታልል ሰዎች አለን።
አንዳዶቻችን ከኃጢአታችን ክብደት የተነሳ የሚያዝናኑ እና የሚያስቁ ስብከቶችን እንጂ፤ ስለ ኃጢአት ነውርነት፤ ስለዘለዓለማዊ ፍርድ፤ ስለንስሐ፤ ተግጻጽ እና
ወቀሳን የያዙ ስብከቶችን መስማት የማንፈልግ እጅግ ብዙዎች ነን። ብዙዎቻችን ደግሞ ትክክለኛውን ነጻ የሚያወጣ የእግዚአብሔር ቃል ባለማግኘታችን
ከኃጢአታችን ለማምለጥ እንደ እግዚአብሔር ቃል ያልሆኑ ወይም የተሳሳቱ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን የምናደርግ፤ በምናደርጋቸው እንቅሥቃሴዎች የኃጢአት
ሥርየት ለማግኘት የምንሞክር፤ ነገር ግን እንቅሥቃሴዎቻችንን ደጋግመን ብናደርጋቸዉም እውነት ስለሌለባቸው እርካታ እና መንፈሳዊ እረፍት ያጣን፤ እውነተኛ
ነጻነት ስለአላገኘን እስከ አሁን የምንቅበዘበዝ እና በኃጢታችን የምንኖር ነገር ግን የምናመልክ ሰዎች አለን።
አንዳዶቻችን ደግሞ ኢየሱስ አድኖናል ኃጢአት ብንሠራም መዳናችንን አይከለክለንም ኢየሱስ ነጻ ስላወጣን በኃጢታችን አንጠየቅም በሚል የሥሕተት ትምህርት
ከንስሀ እርቀን የኃጢአት ባሪያዎች የሆንን የክርስቶስ ተካታዮች የሆንን ከቅድስና እርቀን የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ማዝናኛ ንግግር የምናዳምጥ ምስኪኖች
አለን። ... መጸሐፍ የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ እንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርልንምና የሚያስፈራ ግን የፍርድ
መጠበቅ ተቃዋሚዎችንም ሊበላ ያለው የእሳት ብርታት አለ። የሚለውን ቃል የረሳነው ብዙዎቻችን ነን።
ከላይ የዘረዘርናቸው ነገሮችን የመሳሰሉት ምክንያቶች ሁሉ ኃጢአት የፈጠረብን ጭንቀቶች ናቸው። እነዚህ ምክንያቶች የበለጠ ኃጢአተኛ ያደርጉናል እንጂ
እውነተኛ የሕሊና እረፍት ወይም የነፍስ አርነትን ሊሰጡን አይችሉም።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛውን የኃጢአት ነጻነት የምንጎናጸፈው በምን እንደሆነ ግልጽ በሆነ ቋንቋ ተናግሯል እንዲህ ሲል ... እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት
ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው። ዮሐ 8፡31። ስለ ባርነት ግንዛቤ ላልነበራቸው የአብርሃም ልጆች ሲናገር ...
ኃጢአትን የሚያደርግ የኃጢአት ባሪያ ነው ... እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ አርነት ትወጣላችሁ አላቸው ቁ 34-37። ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥ አሁን
በሕይወታችን አሥሮ ከያዘን ኃጢአት ነጻ ያወጣል ? ? ? ... ይቀጥላል
No comments:
Post a Comment